የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሴት ልጅ ባል እንድታገኝ ተጸለየላት
የባል ጸሎቱ መካሄዱን ተከትሎ ከጌታ የተላኩልሽ ትክክለኛው ባልሽ እኔ ነኝ የሚሉ መልዕክቶች በዝተዋል
በርካቶች ክስተቱን በመተቸት እና በማድነቅ አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው
የጎረቤት ሀገር ኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሴት ልጅ የሆነችው ቻርለኔ ሩቱ ባል ታገኝ ዘንድ ዓላማውን ያደረገ ጸሎት በናይሮቢ ተካሂዷል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ተካሂዷል የተባለው ይህ ጸሎት በአሜሪካዊው ሰባኪ ቤኒ ሂን መሪነት እንደተካሄደ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዚህ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቹጋ እና ባለቤታቸው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
ሰባኪ ቢኒ ሂን ለጸሎት የመጣችሁ ሁሉ እንዲጸለይላችሁ የምትፈልጉትን ንገሩኝ ባሉት መሰረት የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሴት ልጅ የሆነችው ቻርለኔ ባል እንደምትፈልግ ተናግራለች ተብሏል፡፡
በቻይና በወጣትነታቸው ትዳር ለሚመሰርቱ ማበረታቻ ጉርሻ ቀረበ
ሰባኪ ቤኒ ሂንም “ጌታ ሆይ ባል ስጣት፣ ለጥንካሬዋ የሚረዳት ትክክለኛውን ሰው ስጣት፣ እሷ ብቻዋን ይህን ማድረግ አትችልም” ሲል እንደጸለየላት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህን ተከትሎም በርካታ ኬንያዊያን ወጣቶች ስማቸውን እየጠቀሱ ከጌታ የተላኩልሽ ትክክለኛው ባልሽ እኔ ነኝ እያሉ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ እየጻፉ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በርካታ ኬንያዊያን የፕሬዝዳንቱን ልጅ ድርጊት እየወቀሱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ልጅቱ ፍላጎቷን ነው የተናገረችው እያሉ እየደገፏት ይገኛሉ፡፡