በዛምቢያው አዲሱ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት የአፍሪካ መሪዎች ሉሳካ ገብተዋል
ተመራጩ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ሂችልማ ነገ በይፋ ስልጣን ይረከባሉ
እስካሁን የዚምባብዌ፣ ቦትስዋና፣ ማላዊ እና ሌሎች ፕሬዝዳንቶች ዛምቢያ ደርሰዋል
በአዲሱ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት የአፍሪካ መሪዎች ሉሳካ ገብተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሀኬንዴ ሂቺሌማ ምርጫውን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ተመራጩ ፕሬዝዳንት በነገው ዕለት በይፋ ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኤድጋር ሉንጉ ስልጣን እንደሚረከቡ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በዚህ በዓለ ሲመት ፕሮግራም ላይ ለመታደም በርካታ የአፍሪካ አገራት ወደ አገሪቱ መዲና ሉሳካ በመግባት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።
እስካዛሬ ድረስ የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ሞክግዊስቲ ማሲሲ፣ የማላዊው ላዛሩስ ቻክዌራ፣ የዚምባብዌው ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ሌሎችም ዛምቢያ ደርሰዋል።
የ59 ዓመቱ ኢኮኖሚስት ሂቺሌማ በዛምቢያ ፕሬዝዳንት ምርጫ ታሪክ ለአምስት ጊዜ ተወዳድረው በዘንድሮው ምርጫ ለመጀመሪያጊዜ ምርጫውን ማሸነፍ ችለዋል።
ሂቺሌማ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከበርካታ አገራት እንኳን ደስ አለዎት መልዕክት የደረሳቸው ሲሆን ለአብነትም የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ፣ የናይጀሪያ መሀመዱ ቡሀሪ፣ የደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎዛ፣ የታንዛኒያዋ ሳሚያ ሳሉህ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
7 ሚሊዮን ዛምቢያዊያን በተሳተፉበት የዘንድሮው ፕሬዝዳንት ምርጫ ሂችልማ ከ50 በመቶ በላይ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ምርጫውን ማሸነፍ ችለዋል።
በመዳብ ማዕድን የበለጸገችው ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ዛምቢያ ሙስና ትልቁ ችግሯ ነው የሚሉት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሂቺሌማ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያተኩሩ አስቀድመው ተናግረዋል።