ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ዜጎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል
ባይደን ሩሲያ በማንኛውም ቅጽበት ዩክሬንን ልትወር ስለምትችል ሁሉም ነገር ሊለዋወጥ ይችላል ሲሉ አስጠንቀቋል
ሞስኮ “ምእራባውያን የሚሉት ካልሆነ በስተቀረ ወረራ የሚባል ነገር በሀሳቤም የለም” ስትል ተደምጣለች
ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ዜጎች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/NATO/ ሩስያ በቤላሩስ ቀጥታ የተኩስ ልምምዶች ማድረግ መጀመሯ ማስታወቁን ተከትሎ ነው፡፡
ጆ-ባይደን በትናነትናው እለት ኤን.ቢ.ሲ ኒውስ ከተሰኘ የአሜሪካ ሚድያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነገሮች በፍጥነት ሊለዋወጡ ይችላሉ ምክንያቱም ሩሲያ በማንኛውም ቅጽበት ዩክሬንን ልትወር ትችላለች ሲሉም ተናግሯል፡፡
- 4 ሜትር ከሚረዝመው የፑቲንና ማክሮን የውይይት ጠረጴዛ ጀርባ ያለው ሚስጥር ምንድን ነው?
- ሩሲያ በወታደራዊ ዝግጅቷ ለቁስለኞች የሚሆን ደም ማካተቷን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናገሩ
ጦርነቱ ከተጀመረ አሜሪካ ዜጎቿን ለማስወጣጽ ልትቸገር እንደምትችል የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ዜጎች ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት “ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ”ም መክሯል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን አክለው "ጦርነቱ የዓለም ጦርነት ነው፤አሜሪካውያን እና ሩሲያውያን እርስበርስ መታኮስ ሲጀምሩ፤ ሁሉም ነገር ሊቀያየር ይችላል"ም ብለዋል።
እንደ አሜሪካ ሁሉ ጃፓን እና ኔዘርላንድ ዜጎቻቸው ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቋል፡፡
አሜሪካ፣ጃፓን እና ኔዘርላንድ ዜጎቻቸው እንዲወጡ ቢያሳስቡም ወረራ ይፈጸምባታል በተባለችው ዩክሬን በኩል ብዙም የተባለ ነገር የለም፡፡
ዩክሬን ከሀገራቱ በተቃራኒ “ምንም የተለወጠ ነገር የለም ስለዚህም ማንም ሰው ሀገሪቱን ለቆ መውጣት የለበትም” እያለች ነው፡፡
ሞስኮ በአንጻሩ ወረራ የሚባል ነገር በሀሳቤም የለም ስትል ተደምጣለች፡፡
የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ሀሰተኛ ዜና እያሰራጩ ህዝብ በማሸበር ላይ ተጠምዷል ስትልም ነው ሩሲያ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ አማካኝነት የከሰሰችው፡
ሞስኮ እንዲህ ብትልም ግን ዩክሬንን ለመውረር በሚመስል መልኩ ከ100 ሺህ የሚልቁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ በመነገር ላይ ነው፡፡
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊከን የሩሲያ ጠብ አጫሪነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።
የሩሲያ ጥቃት በማንኛውም ቅጽበት ሊጀመር እንደሚችል በተለይም በፌብሩዋሪ 20 የኦሎምፒክ ፍጻሜ ዕለት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች ምልክቶች አሉ ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ምላሽ 3 ሺህ የሠራዊት አባላትን ከኖርዝ ካሮላይና ቀጠና ወደ ፖላንድ አንቀሳቅሳለች፡፡
ይሁንና እነዚህ ወታደሮች ከዩክሬን ወታደሮች ጋር ተሰልፈው ይዋጋሉ ወይስ አይዋጉም ለሚለው ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ከሰኞ ጀምሮ፣ ኪያቭ፣ ሞስኮና በርሊን ሲመላለሱ ነው የሰነበቱት፡፡
የማክሮን ወዲያ ወዲህ ማለት አይቀሬ ነው ለሚባለው ጦርነት የዲፕሎማሲ መፍትሄ ለመሻት እንደነበርም ይገለጻል፡፡