ሀሰን ሼክ መሐመድ በኤምሬቶችና በቱርክ ጉብኝት አድርገው ነበር
በአስመራ ጉብኝት ላይ ያሉት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኤርትራ ያሰለጠነቻቸውን ወታደሮች መጎብኘታቸውን የኤርትራ መንግስት ገለጸ።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሃሙድ ትናንት በኤርትራ በስልጠናላይ የነበሩ የሀገራቸውን ወታደሮች መጎብኘታቸውን የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ አቶ የማነ ገብረመስቀል ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አባላት ላለፉት ሶስት ዓመታት በኤርትራ ስልጠና ላይ ነበሩ።
ለይፋዊ ጉብኝት ባሳለፍነው ቅዳሜ አስመራ የገቡትና መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆን የተኩት አዲሱ ፕሬዝዳንትም እነዚህን የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አባላትን ጎብኝተዋል ተብሏል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ኤርትራ ያሉ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አባላት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በሀሰን ሼክ መሐመድ ሲጎበኙ የሚያሳይ ፎቶ ይፋ አድርገዋል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸው ቅዳሜ ዕለት ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ ማምራታቸውን ገልጸው ነበር።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመራ የገቡት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተላከላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል።
የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ የማነ ገብረ መስቀል እንዳሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሶማሊያውን መሪ አስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሄደው መቀበላቸውንገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በአስመራ ከተማ አራት ቀን እንደሚቆዩ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና በቱርክ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።