አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት “ሽብርተኝነትን በቆራጥነት እንታገላለን” አሉ
ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ሀገራቸውን ሰላም ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንቱ በቀደመው የስልጣናን ዘመናቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመቀናጀት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ከፍተኛ ስራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል
ሶማሊያውያን ሽብርተኝነት በቆራጥነት እንደሚታገሉ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ አስታወቁ።
በባይደዋ እና ዱሳማረብ ከተሞች ጉብኝት ሲያደረጉ የቆዩት ፕሬዝዳንቱ ፤ በጉብኝታቸው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመገናኘት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
“በነበረኝ ጉብኝት ወቅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰብአዊ ቀውሱን ለማቃለል፣ ሽብርተኝነትን በቆራጥነት ለመታገል እና ለጠንካራው የሶማሊያ ህዝብ ስራ ለመፍጠር በጋራ መስራት እንዳለብን ተስማምተዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ከዓመታት በኋላ 10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በዚሁ የስልጣን ዘመናቸው ሀገራቸውን ሰላም ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
በስልጣናቸው የመጀመሪያ ቀናት “ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ማለታቸውም አይዘነጋም።
አዲሱ ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ ከመስከረም 2012 እስከ የካቲት 2017 ድረስ በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመቀናጀትም በተለይም ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ የሚያጋልጥ ከባድ ድርቅን ጨምሮ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉባት ሀገረ ሶማሊያ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ቀላል የቤት ስራ ይዛ እንደማትቆይ በርካቶች የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ሰላማዊ ሶማሊያን እውን ለማድረግ ለወራት በዘለቀው የፖለቲካ ትርምስ እና የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ በአስፈጻሚ ደረጃም ሆነ በማዕከላዊ መንግስት እና በክልል ባለስልጣናት መካከል ያለውን የግንኙነት መሻከር ማስተከከል ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።
የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ምርጫ መዘግየቱ፣ የፖለቲካዊ ሽኩቻ መኖሩ እንዲሁም ከአስር አመታት በላይ መንግስትን ለመጣል ሲዋጉ ከነበሩት የአልሸባብ አማጺያን ጋር የሚደረገው ውጊያ ሀገሪቱን ወደለየለት ቀውስ እንዳያስገባት ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።