የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ከአልሻባብ ጋር እንደራደራለን” አሉ
ፕሬዝዳንቱ “ድርድሩ አክራሪዎችን እና ሁከት በመፍጠር ፍሎጎቶቻቸውን ሊያሳኩ የሚሹ ኃይሎችን አያካትትም” ብለዋል
የአልሻባቡ አዛዥ ማሃድ ካራቴ በቅረቡ “በቪላ ሶማሊያ መቀመጫው ካደረገ ስብስብ ጋር የመደራደር ፍላጎት የለንም” ማለቱ ይታወሳል
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በተርኪዬ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ መንግስታቸው ከአልሻባብ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በአንካራ ሴታ ፋውንዴሽን ኢንስቲትዩት ጉብኝታቸውን የተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
ፕሬዝዳንቱ የቀጠናው ስጋት ከሆነው አልሻባብ ጋር የሚኖረው ቀጣይ ሁኔታን በተመለከተ ለጋዜጠኞቹ በሰጡት ምላሽ “ከአልሸባብ ጋር ለመደራደር የምንችልበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ነገር ግን በትክክለኛው ጊዜ እናደራደራለን”ብለዋል።
“አዲስ መንገድ እየተከተልን ነው፤ ሁሉንም ነገር በሰላም እንጨርሰዋለን” ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጅ ፤ድርድር ሲባል አክራሪዎችን እና ሁከት በመፍጠር ፍሎጎቶቻቸውን ሊያሳኩ የሚሹ ኃይሎችን እንደማያካትት አስረግጠው ተናግረዋል።
መደራደር የምንፈልገው “ሰላም ከሚፈልጉ የአልሻባብ ኃይሎች ጋር ብቻ ነው ሲሉም” ተደምጠዋል ፕሬዝዳንቱ። ምንም እንኳን ሰላም የሚፈልጉት ኃይሎች የትኞቹ ናቸው የሚለው ግልጽ ባያደርጉም።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ፤ አሜሪካ በጥብቅ የምትፈልገውና በአንድ ወቅት የሶማሊያ ከፍተኛ የደህንነት መኮንን የነበረው የአልሻባቡ ምክትል አዛዥ መሃድ ማሃመድ ዓሊ ‘ማሃድ ካራቴ’ በቅረቡ ከእንግሊዙ ቻነል 4 ኒውስ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ “በቪላ ሶማሊያ መቀመጫው ካደረገ ስብስብ ጋር የመደራደር ፍላጎት የለንም” ማለቱ ይታወሳል።
“አንድ እውነታ አለ፤ በምድር ላይ በሰላማዊ መንገድ መርሆቹን እና ፍላጎቶቹን ያሳካ ማንም ሰው የለም” ነበር ያለው ማሃድ ካራቴ።
`ታሊባን አፍጋኒስታንን እንደተቆጣጠረ ሁሉ አልሻባብም ሶማሊያን የመቆጣጠር ዓላማ አለው` ብለዋል ማሃድ ካራቴ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሻባብ ለመምታት በሚል በሳለፍነው ወር 600 የሚሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚልኩ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ፤የአሜሪካ ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉት መግለጻቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት (ቪላ ሶማሊያ) በወቅቱ በትዊተር ገጹ ባጋራው ጽሁፍ "ለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምናደርገው ትግል አሜሪካ ወትሮም ቢሆን ታማኝ አጋራችን ናት" ብሎ ነበር።