ሱዳናዊው ጄነራል መሐመድ ዳጋሎ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በምን ጉዳይ መከሩ ?
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ የሱዳናውያን የውስጥ ችግር መፈታት ያለበት በውጭ ኃይሎች ሳይሆን በራሳቸው ነው ብለዋል
ጄነራል ዳጋሎ፤ የኤርትራ ወደ ኢጋድ መመለስ እንደሚያስደስታቸው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገልጸውላቸዋል
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በትናንትው እለት ለጥቂት ሰአታት በአስመራ ቆይታ አድርገው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
"ሄመቲ" በሚል በቅጽል ስማቸው የሚታወቁትና በሱዳን ፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄነራሉ በአስመራ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው በአንኳር የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መመክራቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ የሱዳኑ ጄነራል በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመመለከተ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ዝርዝር ገለጻ” ያደረጉላቸው ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ "የሱዳን ጉዳይ ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የሱዳን ህዝብ ራሱ ሊፈታው የሚገባ ጉዳይ ነው" ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የሱዳኑ ጀነራል መሐመድ ዳጋሎ (ሄመቲ) በበኩላቸው የኤርትራ ወደ ኢጋድ መመለስ እንደሚያስደስታቸው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገልጸውላቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ በኬንያ በነበራቸው ጉብኝት ኤርትራ ላለፉት በርካታ አመታት ርቃው ወደ ነበረው የቀጠናውን ተቋም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ልትመለስ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
"ቀጣናዊ ውህደትን የሚለውን ሃሳብ ይበልጥ ለማጠናከር ወደ ኢጋድ እንደመለሳለን"ም ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
በተጨማሪም ሁለቱም አካለት በሀገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክረው መቀጠልና መተባባር እንዳለባቸው ሁለቱም መሪዎች መክረዋል፡፡
ከጄነራሉ ጋር አስመራን የጎበኘው የሱዳን ልኡክ የሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ጃፋላ አል-ሐጅ አል-ዓሊን ጭምር ያከተተ ነው፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንደፈረንጆቹ በ2019 የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል-በሽር ለማስወገድ በሱዳን የተለኮሰውን ህዝባዊ አመጽ ደጋፊ እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ይሁን እንጅ ከአል በሽር በኋላ የተመሰረተው የሽግግር መንግስት በ2021 በተደረገው መፈንቅለ መንግስት በድጋሚ መፍረሱን ተከትሎ ሀገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ እንደተናጠች ነው፡፡
በኤርትራ ጉብኝት ያዳረጉት ጄነራል ዳጋሎ በቅርቡ የ2021ዱ መፈንቅለ መንግስት ትክክል እንዳልነበር መናገራቸው አነጋጋሪ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ያም ሆኖ በ2022 መጋባደጃ ላይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ኃይሎች መካካል የተፈረመው ሰነድ ሀገሪቱን ወደ ሲቪልና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ይወስዳታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በትናንትናው እለት አስመራ ገብተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በአስመራ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ በኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተድርጎላቸዋል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስመራን ሲጎበኙ በአንድ አመት ውስጥ የትናንቱ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡
መሪዎቹ በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ነው የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የገለጹት፡፡