ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከቻይና የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ ጋር በአስመራ ተነጋገሩ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ጉብኝቱ በኤርትራ እና ቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያጎለብት መሆኑ ተናግረዋል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቻይና ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸው ይታወሳል
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከቻይና የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሹ ቢንግን ጋር በአስመራ ተናገገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በነበራቸው ቆይታ በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዘለግ ያለ ውይይት ማድረጋቸው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገ/መስቀል አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ሁለቱ ወገኖች በኤርትራ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት መስኮች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ተወያይተዋል” ብለዋል፡፡
ኤርትራ እና ቻይና በቀጣናዊ ትስስራቸው ማዕቀፍ ውስጥ የልማት ትብብር ለማካሄድ መስማማተቸውም ጭምር ተናግረዋል ፡፡
ጉብኝቱ በኤርትራ እና ቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት የሚያችል እንደሆነ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በውይይቱ መናገራቸውም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኤርትራ እና ቻይና በተለያዩ መስኮች በትብብር የሚሰሩ ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በየካቲት በኤርትራ ባደረጉት ይፋወዊ የስራ ጉብኝት፤ በማዕድን ልማት፣ በምጽዋና አሰብ ወደቦች ልማት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና በመሰረተ ልማት ዘርፍ በጋራ ለመስራትም ከስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም በውይይቱ ወቅት ቻይና ለኤርትራ ተጨማሪ የ100 ሚሊየን ዩዋን ድጋፍ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ በወቅቱ መግለጻቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው የቻይናን የ100 ዓመታት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጉዞ እና በዓለም ዐቀፍ ሕጎች ማዕቀፍ ውስጥ ሆና ዓለምን ሚዛናዊ ለማድረግ የምታደርውን ጥረት አድንቀዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ፐሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቻይና ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ እንደላኩላቸውም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር፡፡
ኤርትራ፤ ቻይና በዓለም አቀፍ መድረክ የምታራምዳቸው አቋሞች በመደገፍ የምትታወቅ ሀገር መሆኗም ይታወቃል፡፡