የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኤርትራ ስልጠና እየወሰዱ ስላሉ ሶማሊያውያን ወታደሮች ምን አሉ ?
ፕሬዝዳንቱ ልጆቻቸው ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ኤርትራ ከተወሰዱባቸው የተወሰኑ ወለጆች ጋር ተወያይተዋል
ፕሬዝዳንቱ በስልጠና ላይ ላሉት ወታደሮች “ለስልክ ካርድ መግዣ የሚሆናቸው ገንዘብ ትቼላቸው መጥቻለሁ” ብለዋል
በኤርትራ የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድረገው የተመለሱት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ፤ ወደ ኤርትራ ለወታደራዊ ስልጠና ተልከዋል የተባሉት የሶማሊያ ወጣቶችን በተመለከተ ከተወሰኑ ወላጆች ጋር መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ረቡዕ እለት በትዊተር ገጹ የለቀቀው ቪዲዮም ፕሬዝዳንቱ የተወሰኑ ወላጆችን ተቀበለው ሲያነጋገሩ የሚያሳይ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከወላጆች ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለልጆቻቸው ህልውና ሲያወሩዋቸው ይደመጣሉ፡፡
“በዒድ አልአድሃ ማግስት ኤርትራ ወደ ሚገኘው ማሰልጠኛ ማእከል ህጄ ልጆቻችሁን አይቻለሁ፤ ስዕሎቹን ተመልክታችሁ ይሆናል”ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ በቪዲዮው ወላጆቹን ሲናገሩ የሚደመጡት፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ለስልክ ካርድ መግዣ የሚሆናቸው ገንዘብ ትቼላቸው ነው የመጣሁት፤ ስልክ እንዲደውሉላችሁም ነግሬያቸዋለሁ፤ ዛሬ ወይም ነገ የሚደውሉላችሁ ይሆናል”ብለዋል፡፡
አባት እንደሆኑ እና የልጅ ልጅ እንዳለቸው የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ የወላጆች ህመም ጠንቅቀው እንደሚረዱም ተናግረዋል፡፡
“ልጆቻችሁ ከእናንተ ከተለዩ በኋላ፤ በተለይም የሚገኙበት ቦታ ካለማወቃችሁ ጋር ተዳምሮ ሊኖር የሚችል ህመም ይገባኛል”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡ወላጆቹ በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ የልጆቻቸውን ህልውና እንዲያውቁ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል፡፡
ከወላጆቹ አንዷ እናት ልጆቸው ረቡዕ እለት እንደደወለላቸው ተናግረዋል፡፡
በከፈተኛ የሃዝን እና ተስፋ በታጀበው ውይይት መሃል አንድ ወላጅ በልጃቸው ናፍቆት ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ፤ ፕሬዝዳንቱ ሲያጽናኑዋቸውም በቪዲዮው ይታያል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የሚያለቅሱትን ወላጅ ሲያጽናኑ “ አይዞን፤ የደስታ ቀናት እየመጡ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡እንደፈረንጆቹ ከሃምሌ 9 እስከ 12 በኤርትራ ጉብኝት ያደጉት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኤርትራ ያሰለጠነቻቸውን ወታደሮች መጎብኘታቸውን የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረመስቀል ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
ቃል አቀባዩ አቶ የማነ ገብረመስቀል ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አባላት ላለፉት ሶስት ዓመታት በኤርትራ ስልጠና ላይ ነበሩ።
የሰማሊያ ወታደሮችን ጉዳይ በተመለከተ ሶማሊያም ሆነ ኤርትራ ለረዥም ጊዜ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የነበረ ቢሆንም ፤ በቅርቡ ተሰናበቱት የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ባስረከቡበት ወቅት 5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው ይታወሳል፡፡