በኬንያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ለቻሉት ኬንያውያን ሁሉ ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል
ኡሁሩ ኬንያታ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመፈጸም ቃል እንደሚገቡ ገልጸዋል
በኬንያ አዲስ ፕሬዝዳንት መመረጣቸውን ተከትሎ የስልጣን ርክክቡ ሰላማዊ እንዲሆን አስፋጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ፡፡
ኡሁሩ ትናንት ማምሻው በቴሌቭዥን መስኮት ባደረጉት ንግግር፤ ስልጣን ሲይዙ በገቡት ቃል የህግ የበላይነትን እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዊልያም ሩቶ መመረጥ ያጸናበት ብይን እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
ኡሁሩ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመፈጸም ቃል እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
የስልጣን ርክክቡን በተሰካ ሁኔታ ለማከናወን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኮሚቴ እንደፈረንጆቹ ከነሐሴ 10 ቀን 2022 ጀምሮ አስፈላጊ የሚባሉ የዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ፡፡
"ወደ ቀጣዩ አስተዳደር የሚደረገውን ሽግግር ሰላመዊ እንዲሁን ፍላጎቴ ነው እናም እነዚህን ሂደቶች ለማመቻቸት ሁሉም አስፈላጊ ትዕዛዞች ቀድሞውኑ ተሰጥተዋል"ም ነው ያሉት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፡፡
እስካሁን ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ እስካሁን የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕከት ያላስተላለፉት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ለቻሉት ኬንያውያን ሁሉ ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል፡፡
ዲሞክራሲ ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው ያሉት ኡሁሩ፣ የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ የዴሞክራሲ ተቋማትን በማክበር የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኬንያ በተካሄደው ፕሬዝዳናታዊ ታዊ ምርጫ የዊሊያም ሩቶ አሸናፊነትን ያጸናበት የመጨረሻው ብይን በትናንትናው እለት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ፍርድ ቤቱ ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ አሸናፊነት ያጸናው የራይላ ኦዲንጋን ክስ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡
በምርጫው ጠባብ በሆነ ውጤት የተሸነፉትና ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ሲከራከሩ የቆዩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋም ውጤቱ በጸጋ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
ራይላ ኦዲንጋ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ባንስማማበትም የፍርድ ቤቱ የዛሬ ብይን እናከብራለን” ብለዋል፡፡በኬንያ ህግ መሰረትም ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፊታችን መስከረም 3 ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ሲጂቲኤን ዘግቧል።