ዋትስአፕ በሐምሌ ወር ብቻ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የህንድ አካውንቶችን አገደ
የፈጣን መልእክት መተግበሪያ ዋትስአፕ፤ በሐምሌ ወር ብቻ 574 የቅሬታ ሪፖርቶችን መቀበሉ አስታውቋል
ዋትስአፕ፤ በሰኔ ወር በህንድ ብቻ 2 ነጥብ 21 ሚሊዮን አካውንቶችን አግዶ ነበር
ዋትስአፕ በሀምሌ ወር ብቻ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የህንድ አካውንቶችን ማገዱን አስታወቀ፡፡
እገዳው በዚህ አመት ከፍተኛ መሆኑ ባለቤትነቱ የሜታ ኩባኒያ የሆነው ታዋቂው የፈጣን መልእክት መተግበሪያ ዋትስአፕ ገልጿል።
የእስያዋ ሀገር ጥብቅ የአይቲ ህጎች ለትላልቅ ዲጂታል ፕላትፎርሞች በየወሩ ሪፖርቶችን እንዲያወጡ የሚያደረግ አሰራር መዘርጋታቸው የሚታወቅ ነው።
በሰኔ ወር በተሰራጨው ረቂቅ ህግ ፍርድ ቤት በሚያዘበት ወቅት፤ የመጀመሪያውን የመረጃ ምንጭ ማንነት ለመለየት እንዲቻል ጉልህ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ የመልእክት መላላኪያ መድረኮች ፈቃድ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ነው፡፡
ረቂቁ፤ የተጠቃሚዎችን ይግባኝ የሚሰማ ቡድን እንዲቋቋም የሚል ሀሳብ ማቅረቡም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
በዚህም መሰረት ከተከለከሉት አካውነቶች ውስጥ 1 ነጥብ 42 ሚሊዮን የሚሆኑት የተጠቃሚዎች ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት ቀድመው ታውቀው የታገዱ መሆናቸው ዋትስአፕ ይፋ አድርጓል፡፡
እገዳው የተደረገው፤ በኩባንያው የቅሬታ መስጫ ቻናል በኩል በደረሱ ቅሬታዎችን ተከትሎ በተደረገው ልየታ መሆኑም ነው ዋትስአፕ የገለጸው፡፡
ዋትስአፕ፤ በሐምሌ ወር ብቻ 574 የቅሬታ ሪፖርቶችን መቀበሉም አስታውቋል፡፡
በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደራጃ ሀሰተኛ ዜናዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በማሰራጨት ሲተች የነበረው ዋትስአፕ ፤በሰኔ ወር በህንድ በቻ 2 ነጥብ 21 ሚሊዮን አካውንቶችን ማውረዱ አይዘነጋም፡፡