የታዋቂው የነጻነት ታጋይ ቼኩ ቬራ ልጅ ህይወት አለፈ
አርጀንቲናዊው አብዮተኛ ቼኩቬራ አራት ልጆች ነበሩት
ከቼኩ ቬራ ልጆች መካከል አንዱ የነበረው ካሚሎ በ60 ዓመቱ ማረፉ ተሰምቷል
የታዋቂው የነጻነት ታጋይ ቼኩ ቬራ ልጅ ህይወቱ አለፈ።
በትውልድ አርጀንቲናዊ የሆነው የማርክሲስት አስተሳሰብ አቀንቃኝ የሆነው ኤርኔስቶ ቼኩ ቬራ ቅኝ ግዛት እና ወረራ የተፈጸመባቸውን ሀገራት በማገዝ ይታወቃል።
ይህ አብዮተኛ ሰው በተለይም የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ሀገራትን ለማድቀቅ ከቀድሞው የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ ጋር ለረጅም ዓመታት በትግል አሳልፏል።
ዓለም አቀፍ የጸረ ቅኝ ግዛት ታጋይ እንደሆነ የሚነገርለት ቼኩ ቬራ የአራት ልጆች አባት ነበር ተብሏል።
ከልጆቹ መካከል አንዱ የሆነው ካሚሎ ቼኩ ቬራ በተወለደ በ60 ዓመቱ በስትሮክ ( ወደ ጭንቅላት ደም መፍሰስ) በሽታ ተጠቅቶ ህይወቱ እንዳለፈ ቢቢሲ የወቅቱ የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ዲያዝን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት " በካሚሎ ሞት አዝኛለሁ፣ የአባቱን የቼን ሀሳብ አድናቂ እና አራማጅ ነበር" ብለዋል።
ካሚሎ ቼ ህይወቱ ያለፈው በቬንዙዌላ መዲና ካራካስ እንደሆነም ተገልጿል።
ሟቹ ካሚሎ በኩባ በአባቱ ስም የተሰየመው የቼኩቬራ ጥናት ማዕከልን በመምራት ላይ የነበረ ሲሆን ማዕከሉ የአባቱን አስተሳሰብ፣ ልምድ እና የህይወት ተሞክሮውን ለሌሎች በማስፋት ይታወቃል።
በሽምቅ ውጊያ ታዋቂ የሆነው ቼጉቬራ የህክምና ሙያ ያጠና ሲሆን አብዛኛው የህይወት ዘመኑን የኮሙኒስ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ሀገራትን በሽምቅ ውጊያ ስልጠና ፣ በጦር መሳሪያ እና የስለላ መረጃዎችን በመስጠት በመደገፍ ይታወቃል።