የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ለምን አፍሪካ ቀንድ ላይ አይናቸውን ጣሉ?
አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት ተመድ እና የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ሾመዋል
ሀገራትና ተቋማት ከአፍሪካ አህጉር ልዩ አምባሳደር የሾሙት በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሲሆን ይሄ መሆኑ ደግሞ የብዙዎች ጥያቄ ነው
አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት ተመድ እና የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ሾመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፈረንሳይ፣ ቱርክ ፣አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን የጦር ሰፈር ሲገነቡ ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ በዚሁ አካባቢ ባሉ ሀገራት ውስጥ የጦር ሰፈር ለመገንባት በሂደት ላይ ናቸው።
እነዚህ ሀገራት እና ተቋማት በአፍሪካ አህጉር ካሉ ክፍሎች ውስጥ ልዩ አምባሳደር የሾሙት በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሲሆን፤ ይሄ መሆኑ ደግሞ የብዙዎች ጥያቄ ነው።
አል ዐይን አማርኛ እነዚህ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ለምን የተለየ ትኩረት ሊሰጡ እንደቻሉ ምሁራንን አነጋግሯል።
ሎግማን ኦስማን በተመድ የአፍሪካ ቢሮ የደህንነት አማካሪ ሲሆኑ የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮችን በመተንተን ይታወቃሉ።
ሎግማን ኦስማን አል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት፤ ባለጸጋ ሀገራትን ጨምሮ መላው የዓለማችን ሀገራት ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት፣ ሰፊ የገበያ አቅም ያለው ህዝብ ብዛት መኖር እና አካባቢው ከሌሎች አህጉራት ጋር ያለው ቅርበት ሀገራቱን ለአፍሪካ ትኩረት እንዲያደርጉ አድርጓል ብለዋል።
እነዚህ ሀያላን ሀገራት ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣታቸው በራሱ ችግር ባይኖረውም የፍላጎት መወሳሰብ እና በሉዓላዊ ሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ለይ ጣልቃ መግባትን ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን አክለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሀያላን ሀገራት ትኩረት መሳባቸውን በመረዳት ግልጽ የሆነ ስጋትን ሳይሆን መተማመንን ሊያዳብሩ የሚችሉ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሊከተሉ እንደሚገባም ባለሙያው ተናግረዋል።
ግልጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲቀረጽ እና ሲተገበር የሀያላን ሀገራትን እና የጎረቤት ሀገራትን ጣልቃ ገብነት የመጋለጥ እድሎችን ሊቀንስላቸውን እንደሚችልም ባለሙያው አክለዋል።
የሀያላን ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ልዩ የጦር መንደር መገንባታቸው በአስተናጋጅ ሀገራቱ ፍላጎቱ ይወሰናል የሚሉት ሎግማን ኦስማን ሀገራቱ ጥቅም እስካስገኘላቸው ድረስ ሊፈቅዱ ይችላሉም ብለዋል።
አፍሪካ ህብረትም ሆነ ማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የበለጸጉ ሀገራት የጦር መንደር እንዳይገነቡ ሊከለክል አይችልም ነገር ግን አስተናጋጁ ሀገር ጥቅሙን እና ጉዳቱን አይቶ ሊወስን ቢችልም ሀያላኑ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በሚያደርጓቸው ውስብስብ እንቅስቃሴዎች ሰለባ ላለመሆን ግን መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካ እና እስያ ጉዳዮች መምህር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ በበኩላቸው አፍሪካ ቀንድ በዓለም ላይ ካሉ ተፈላጊ ቦታዎች መካከል አንዱ መሆኑን አል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በየመን እና ሳውዲ አረቢያ አካባቢ ያለው ባብኤል መንደብ፣ የኢራኑ ሆርሙዝ፣ የግብጹ ስዊዝ ካናል እና በእስያ እና ላቲን አሜሪካ ያሉ ሌሎችም ስፍራዎች በዓለማችን እጅግ ጠቃሚ አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ሳሙኤል ሀያላን ሀገራት ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ወደነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ያደርጋሉም ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድም በሀያላኑ ሀገራት ትኩረት የሚደረግበት ቦታ በመሆኑ ሽብርተኝነትን፣ የባህር ላይ ዝርፊያ እና ሌሎች ጉዳዮች ጥቅሞቻቸውን እንዳያሳጣቸው በመስጋት ወታደራዊ የጦር ሰፈርን ከመገንባት ጀምሮ ልዩ ልዑክ እስከመሾም መድረሳቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የዓለማችን ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የአጋር ሀገራት መሪዎች በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ለጥቅማቸው ስጋት የሆነ ሀገር ስርዓትን እንዳይረጋጋ በሚል ቡድኖችን እና አማጺዎችን እስከመርዳት ሊደርሱ እንደሚችሉም ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ዋና ዋና የዓለማችን ሀያላን ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ትኩረት ቢያደርጉም ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ደግሞ አዳዲስ ሀገራት ለአብነትም እንደ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ኢራን ፣ግብጽ እና መሰል ሀገራትም ለቀንዱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
እነዚህ ሀያላን ሀገራት ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅላቸው የሚችሉ ታዛዥ ሀገራትን መያዝ ዋነኛ ትኩረታቸው በመሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከጥገኝነት ሊያወጧቸው የሚችሉ ስራዎችን ከወዲሁ ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።