የዩክሬን ግዛት የነበሩት ሉሃንስ፣ኬርሰን፣ ዛፖሮዚየ እና ዶንቴስክ ግዛቶች በይፋ ሩሲያን ተቀላቅለዋል
ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ በይፋ ጠቀለለች፡፡
ሩሲያ ባለፈው የካቲት ወር ላይ ለልዩ ዘመቻ በሚል ነበር ጦሯን ወደ ዩክሬን ግዛቶች የላከችው፡፡ በወቅቱ ሩሲያ ጦሯን ለመላኳ ዋነኛው ምክንያት ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
ይሄንን ተከትሎም ሩሲያ 20 በመቶ የዩክሬን ግዛት የሆኑ አራት ግዛቶችን ከያዘች በኋላ ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ በሉሃንስ፣ኬርሰን፣ ዛፖሮዚየ እና ዶንቴስክ ግዛቶች ወደ ሩሲያ መቀላቀል የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ደምጽ ሰጥተዋል፡፡
የህዝበ ውሳኔው ደምጽ ውጤት ከትናት በስቲያ ይፋ የሖነ ሲሆን የአራቱ ግዛቶች 96 በመቶ ነዋሪዎቹ ወደ ሩሲያ መቀላቀል እንደሚፈልጉ መወሰናቸውን ተከትሎ በይፋ በዛሬው ዕለት የሩሲያ አንድ አካል መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ፑቲን በፊርማቸው እንዳጸደቁ ራሺያ ቱዳይ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ግዛት የነበሩት ሉሃንስ፣ኬርሰን፣ ዛፖሮዚየ እና ዶንቴስክ ክልል መሪዎች በተገኙበት የሩሲያ አካል መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከፊርማው ስነ ስርዓት በኋላ በሞስኮ ጎዳናዎች “ሩሲያ፣ ሩሲያ፣ ሩሲያ” የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ ነበርም ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አራቱን ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የሚያረጋግጠውን ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ “ ዩክሬን ጦርነቱ እንዲቆም ከፈለገች የጥላቻ ድርጊቶቿን በማቆም ወደ ድርድር እንድትመጣ ጥሪዩን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የየዩክሬን አካል የነበሩ ክልሎች በምርጫቸው ወደ ሩሲያ መምጣት እንፈልጋለን ብለዋል ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሞስኮ ምርጫቸውን በማክበር ትጠብቃቸዋለች፣ እነዚህን ግዛቶች መንካት ማለት ሩሲያን መንካት ነውም ሲሉ አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከሰሞኑ ጥቃት የደረሰበት የኖርድ ስትሪም ጋዝ ማስተላፊያ ጥቃት የደረሰበት በአሜሪካ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ የነዳጅ ማስተላለፊያው ላይ ጥቃት ያደረሰችው በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጥላ ያሰበችውን ያህል ጉዳት ባለማድረሷ በመበሳጨቷ እንደሆነም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል፡፡