በናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የተፋሰሱ ሀገራት መሪዎች ጉባዔ እንዲያደርጉ የኡጋንዳ ፕሬዝደንት ሀሳብ ማቅረባቸው ተገለፀ
ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከጠ/ሚ ዐቢይ የተላከ መልዕክት ለኡጋንዳ ፕሬዝደንት አደረሱ
የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዶ/ር ስለሺ ለፕሬዝደንት ሙሴቬኒ አብራርተዋል
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለኡጋንዳ ፕሬዝደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ማድረሳቸውን የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ስለሚደረገው የሰብዓዊ እና የመልሶ ማቋቋም ተግባር ፣ ስለ ሕዳሴው ግድብ ፣ ስ ቀጣዩ የኢትዮጵያ በብሔራዊ ምርጫ እና ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ውዝግብ ለፕሬዝደንት ሙሴቬኒ ገለፃ ማድረጋቸውንም ዶ/ር ስለሺ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸውንም ነው ዶ/ር ስለሺ የጠቆሙት፡፡ በተጨማሪም ከወንዙ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በአጨቃጫቂ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የናይል ተፋሰስ ሀገራት መሪዎች ጉባዔ እንዲያደርጉ ፕሬዝደንቱ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ በዚህም የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች በመሪዎች መመሪያ ሊሰጣቸው እንደሚችል ፕሬዝደንቱ ሀሳብ ማንሳታቸውን ዶ/ር ስለሺ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከኡጋንዳ አስቀድመው ፣ በቅርቡ በደቡብ ሱዳን እና በሩዋንዳም ተመሳሳይ ጉብኝት በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መልዕክት አድርሰዋል፡፡
በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከሚያደርጉት ድርድር ባለፈ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጫና ለማሳደር የተለያዩ አማራጮችን መጠቀማቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሦስቱም ሀገራት ወደ ተለያዩ የጎረቤት እና ሌሎች ሀገራት ልዑካንን በመላክ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ፣ በዚህ ረገድ በይበልጥ ግብፅ እና ሱዳን በርካታ ሀገራትን በመዞር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት በተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን አድርገዋል፡፡
የግብፅ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ትናንት ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም በካርቱም የተወያዩ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የግድቡን የውሃ ሙሌት “ያለአስገዳጅ ስምምነት እንዳታከናውን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ ግብፅ እና ሱዳን አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልጉ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ አስገዳጅ ስምምነት የመፈረም ፍላጎት የላትም፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን ከግድቡ በተጨማሪ ከፍተኛ የድንበር ውዝግብ ውስጥም ይገኛሉ፡፡