ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ሆኑ፡፡
የሪፓብሊካኑ የበላይነት ያለበት የአሜሪካ ሴኔት በኮንግረሱ ጸድቆ የቀረበለትን ሁለቱንም የፕሬዝዳንቱን ክሶች ውድቅ አድርጓል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ስልጣንን ያለአግባብ ተጠቅመው ከዩክሬን ጋር ፈጽመዋል የተባለው ክስ 52 ለ 48 በሆነ ድምጽ ሲወድቅ፣ በኮንግረሱ ስራ ጣልቃ ገብተዋል የሚለው ሁለተኛ ክስ ደግሞ 53 ለ 47 በሆነ ድምጽ ነው ውድቅ የሆነው፡፡
በመሆኑም የፕሬዝዳንቱ ስልጣን በቀጣዩ ህዳር በሚካሄደውና 150 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች እንደሚሳተፉ በሚጠበቀው የሀገሪቱ ምርጫ የሚወሰን ይሆናል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣን እንዲወርዱ ክስ ከተመሰረተባቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ለድጋሚ ምርጫ መወዳደር የሚፈልጉ የመጀመሪያው የሀገሪቱ መሪ ናቸው፡፡
ከፕሬዝዳንት ትራምፕ በፊት በአሜሪካ ታሪክ መሰል ከስልጣን የማውረድ ክስ (ኢምፒችመንት) ያጋጠማቸው ሁለት ፕሬዝዳንቶች ብቻ ናቸው፤ ቢል ክሊንተን በ1999 እና አንድሪው ጆንሰን በ1868፡፡ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ደግሞ በ1974 ከመከሰሳቸው በፊት በፈቃዳቸው ከስልጣን ወርደዋል፡፡
ይሄን መሰል ክስ የመፈጸሙ እድል በጣም ጠባብ ሲሆን ክሱም ከወንጀል ይልቅ በዋናነት ፖለቲካዊ ግብ ያነገበ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አሁን የምርጫ ቅስቀሳቸውን ከዚሁ የክስ ሂደት ጋር በማያያዝ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ የክሱ ሂደት የዲሞክራቶች የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ነገር ግን መቼም አያሸንፉኝም ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ዝተዋል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ