የአረብ ኤሜሬትስ ፕሬዝዳንት በሩስያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ሼክ መሀመድ ቢንዛይድ በመጪው ሳምንት በሩስያ የሚካሄደውን የብሪክስ አባላት ጉባኤ ለመጀመርያ ጊዜ ይሳተፋሉ
ብሪክስን ከተቀላቀሉ አዲስ አባል ሀገራት መካከል ዩኤኢ በጥቅል ሀገራዊ ምርት እድገቷ ሁለተኛ ነች
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢንዛይድ አልናህያን በመጪው ሳምንት ሰኞ በሩስያ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ቀጣዩ ቀን ከሚጀመረው የብሪክስ አባል ሀገራትጉባኤ በፊት በሩስያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እና ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚመክሩ ተነግሯል።።
ከፑቲን ጋር በሚኖራቸው ውይይትም በሁለትሽ ግንኙነት፣ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በኢነርጂ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም በቅርቡ የብሪክስ አባል ሀገራት ስብስብን ከተቀላቀሉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ዩኤኢ በ16ተኛው የአባል ሀገራቱ ጉባኤ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በመሪዋ የምትሳተፍ ይሆናል።
“ብሪክ” በሚል ስያሜ ቻይና ህንድ ሩስያ እና ብራዚልን ይዞ የተመሰረተው ስብስብ የመጀመሪያውን የመሪዎች ጉባኤ በሰኔ ወር 2009 በሩሲያ አስተናጋጅነት ነበር ያካሄደው፡፡
በ2011 የደቡብአፍሪካን መቀላቀል ተከትሎ ስያሜውን ወደ “ብሪክስ” የቀየረ ሲሆን፤ በዚህም እስከ 2023 ድረስ አምስት አባላቱ የአለማችን 40 በመቶ ህዝብ እና ከ30 በመቶ በላይ ኢኮኖሚን የሚያንቀሳቅሱ ናቸው፡፡
በ2023 በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው 15ተኛው የአባል ሀገራቱ ጉባኤ ላይ አዳዲስ አባላቶችን ለመቀበል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ጥምረቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ አርጀንቲና፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ሳውዲ አረቢያ እና ኢራን ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡
ከጥር 2024 ጀምሮ ብሪክስን የተቀላቀሉት ሀገራት የቡድኑን አለማቀፍ ተጽዕኖ ለማሳደግ እንደሚያግዙ ይጠበቃል።
ከዚህ ውስጥ 948.05 ቢሊየን ዶላር አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት ያላት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከሳኡዲ አረብያ በመቀጠል አዲስ ቡድኑን ከተቀላቀሉ ሀገራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ናት፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የብሪክስ ስብስብ በአንጻራዊነት ፈጣን እድገት ካስመዘገቡት ምዕራባውያን ጋር ሲነጻጸር በመጪዎቹ አመታት የአለም አብዘሀኛው ኢኮኖሚ እድገት የሚያመነጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአባል ሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣት በውጫዊ ተጽዕኖ እና ጣልቃገብነት ጥገኛ የማይሆን የኢኮኖሚ ሉአላዊነት የሚኖረው ስርአትን ለመገንባት ያግዛል ነው ያሉት፡፡