የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን በመገኘት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን ሸኝተዋል
ኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያሳድጉ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን በመገኘት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን ሸኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ውዱ ወንድሜ ሼክ ሙሀመድ ቢን ዘይድ በኢትዮጵያን በነበራቸው ቆይታ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የጋራ የትብብር አድማሳችንን ማስፋት እንቀጥላለን" ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ችግኝ የተከሉት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የሳይንስ ሙዚየምንም ጎብኝተዋል።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር አዲስ አበባ የገባው ልኡክ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም የመከረ ሲሆን በ17 ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረሙም ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2004 በኤምሬትስ ቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ስትከፍት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ ግንኙነት ባለፉት ሁለት አስርት እየጎለበተ ሄዷል።
በ2010 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችው አቡ ዳቢ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣn ከመጡ ወዲህ ከምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራለች።
ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ ያደረገችው ድጋፍ 5 ቢሊየን ዶላር ተሻግሯል፤ በኢትዮጵያ የምታደርገው ኢንቨስትመንትም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
የሀገራቱ የንግድ ልውውጥም በ2022 ብቻ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በ2018 የአቡዳቢ ልኡል አልጋወራሽ እያሉ ኢትዮጵያን የጎበኙት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከትናንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝትም የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ፣ ማህበረ ኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያጠናክር ተገልጿል።