የራሽያ መከላከያ ሚኒስትር ሃገራቸው በማዘጋጀት ላይ ያለችውን የኮሮና ክትባት ተከተቡ
በክትባቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ የሙከራ ሂደቶች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል መባሉ የሚታወስ ነው
ፍላጎቱ ያላቸው የሃገሪቱ ጦር መኮንኖች ቀድመው ክትባቱን ይወስዳሉ ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይ ሁሉም የጦሩ አባላት ይከተባሉ ብለዋል
የራሽያ መከላከያ ሚኒስትር ሃገራቸው በማዘጋጀት ላይ ያለችውን የኮሮና ክትባት ተከተቡ
የራሽያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ሃገራቸው በማዘጋጀት ላይ ያለችውን ስፑትኒክ ቪ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተከተቡ፡፡
ሚኒስትሩ “ስፑትኒክ ቪ”ን የተከተቡት የክትባቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ የሙከራ ሂደቶች አበረታች ውጤቶችን አስገኝተዋል በተባለበት በትናንትናው ዕለት ነው፡፡
ሙከራውን የተመለከቱ የጥናት ውጤቶች ትናንት “ላንሴት” በተሰኘው ዓለም አቀፍ የህክምና ጉዳዮች መጽሄት ላይ ወጥተዋል፡፡
ክትባቱ እምብዛም የጎንዮሽ ጉዳትን ሳያስከትል ሰውነት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችልበትን ጸረ እንግዳ አካል (አንቲቦዲ) ለማዘጋጀት ስለማስቻሉም ነው ጥናታዊ ጽሁፎቹ ያመለከቱት፡፡
ራሽያ ኒውስ 24 ሚኒስትሩ ሲከተቡ የሚያሳይ ቪዲዮን ለቋል፡፡ በህንድ የራሽያ ኤምባሲም ቪዲዮውን በትዊተር የማኅበረሰብ ገጹ አጋርቶታል፡፡
በመጀመሪያ ፍላጎቱ ያላቸው የሃገሪቱ ጦር የህክምና አባላት እና የጦር መኮንኖች ክትባቱን በሙሉ ፍቃደኝነት እንደሚወስዱ የተናገሩት ሚኒስትሩ በቀጣይ ሁሉም የጦሩ አባላት እንደሚከተቡ ገልጸዋል፡፡
ራሽያ ከአንድ ወር በፊት ነበር የቫይረሱን ክትባት ማግኘቷን ያስታወቀችው፡፡ በወቅቱ ራሳቸው ፕሬዝዳንት ፑቲንም ነበሩ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው አዲስ የተባለውን ግኝት ያበሰሩት፡፡
ልጃቸውን ጨምሮ ራሳቸው ጭምር ክትባቱን ስለመውሰዳቸውም ነበር ፑቲን በወቅቱ ያስታወቁት፡፡ ከዛ ወዲህም የሞስኮው ከንቲባ ሰርጌይ ሶቢያኒንን ጨምሮ ሌሎች የሃገሪቱ ባለስልጣናት የዓለም ጤና ድርጂት ገና ብዙ መፈተሽ ይጠበቅበታል ያለውን “ስፑትኒክ ቪ”ን ተከትበዋል፡፡