‹‹የዓለም ጤና ድርጅትን ማውገዝ ኮሮናን እንዲስፋፋ ማድረግ ነው›› የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
‹‹የዓለም ጤና ድርጅትን ማውገዝ ኮሮናን እንዲስፋፋ ማድረግ ነው›› የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የዓለም ጤና ድርጅትን በዚህ ሰዓት ማውገዝና ማጥቃት ኮሮናን ለማስፋፋት በር መክፈት ነው ሲሉ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ገለጹ፡፡ ላቭሮቭ አር.አይ.ኤ ኖቮሰቲ ከተባለ የሃገራቸው መገናኛ ብዙሃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በመጥቀስ ሲጂቲኤን እንደጻፈው አሁን ላይ አንዳንድ ሃገራት ለወረርሽኙ ትክክለኛ ምላሽ አለመስጠታቸው እንዳይታወቅባቸው ጣታቸውን በጀኔቩ ተቋም ላይ እየቀሰሩ ነው ብለዋል፤ ይህ ደግሞ አስነዋሪና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንደሆነ በማንሳት፡፡
"እኔ ይህንን ወረርሽኝ ድጋፍ ለማግኘት ብዬ ፖለቲካዊ ላደርግ አልችልም፤ ይህንን እያደረጉ ያሉ ግን እንዳሉ ምልክቶችን እያየሁ ነው፡፡ ሃገራቱ መስራት ያለባቸውን በጊዜ ባለመስራታቸው የመጣውን ችግር ለመሸፈን ነው በዓለም ጤና ድርጅት ላይ እያሳበቡ ያሉት" ብለዋ ሰርጌ ላቭሮቭ፡፡
ከ አራት አስርት ዓመታት በላይ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ላቭሮቭ "የዓለም ጤና ድርጅት ፍጹም አይደለም፤ሊሳሳት ይችላል፤ ማንም ትክክል የለም፤ ነገር ግን ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፤ እየመራና እያስተባበረ ነው የሚገኘው" ሲሉ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን አውግዘዋል፡፡
የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ የሚወሰነው በአባል ሃገራቱ ነው ያሉት ላቭሮቭ ተቃውሞዎቹ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህንን አስተያየት የሰጡት አሜሪካ ለድርጅቱ የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን ተከትሎ ነው፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን