ፕሬዝዳንት ፑቲን በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ የሚገኝ የድሮን ማምረቻ ማዕከልን ጎብኝተዋል
ፕሬዝዳንት ፑቲን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ድሮን እንዲመረት አዘዙ፡፡
ለጥቂት ቀናት በሚል የተጀመረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ እዚህ ደርሷል፡፡
ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ ሁለቱም ሀገራት ቴክኖሎጂዎችን አብዝተው በመጠቀም ላይ ሲሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ደግሞ በትንሽ መስዋዕትነት ብዙ ድሎችን ያስገኛሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ባለ የሰው አልባ አውሮፕላን አልያም የድሮን ማምረቻ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ሩሲያ የድሮን ምርቶችን ባለፈው ዓመት ከነበረው 10 እጥፍ እንዲጨምር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ተብሏል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የሩሲያ ጦር ባሳለፍነው ዓመት 140 ሺህ አዲስ ድሮኖችን የታጠቀ ሲሆን ህ ቁጥር በዚህ ዓመት ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን እንዲያድግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝቱ ወቅት ሰው አልባ አውሮፕላኖች የጠላትን እንቅስቃሴ ለመለየት፣ ወታደራዊ መጋዝኖችን ለማውደም እና ከዩክሬን የሚነሱ ድሮኖችን ለማምከን ጥቅም ላይ ለማዋል ይረዳሉ ማለታቸውም ተገልጿል፡፡
ዩክሬን ድሮኖችን በመጠቀም በሩሲያ ግዛቶች ላይ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ ስትሆን ወታደራዊ ማዕከላት፣ የነዳጅ ማጣሪያዎች እና ሌሎች ኢላማዎችን እየመታች መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ፑቲን ሩሲያ በወታደሮች ብዛት ከአሜሪካ እና ህንድ እንድትበልጥ አዘዙ
የአሜሪካ አየር ሀይል ከፍተኛ አመራር ከሰሞኑ የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ጦርነት በፊት ከነበረው የበለጠ ጠንካራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን የአየር ላይ ጥቃቶች ለማክሸፍ በሚል ከምዕራባዊን ሀገራት ኤፍ-16 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን እንዲሰጣት ከጠየቀች በኋላ ሀገራት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አሁን ደግሞ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ እንዲደረግላት እና በሩሲያ ምድር ጥቃት ማድረስ እንድትችል ሀገራት ይሁንታ እንዲሰጧት እየጠየቀች ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት ሲፈቅዱ የተወሰኑት ደግሞ በመቃወም ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው የኔቶ ሀገራት ዩክሬን በረጅም ሚሳኤሎች ሩሲያን እንድታጠቃ ከፈቀዱ የቀጥታ ጦርነት ከኔቶ ጋር ሊጀመር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡