አሜሪካ የሩሲያን መከላከያ ይደግፋሉ ባለቻቸው 42 የቻይና ኩባንያዎች ላይ የንግድ ገደብ ጣለች
ዋሽንግተን ሰባት የሌሎች ሀገራት ኩባንያዎችንም በቁጥጥር ዝርዝሩ ውስጥ አካታለች
ሀገሪቱ የአሜሪካ መሰረት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለሩሲያ ከሸጣችሁ እርምጃ እወስዳለሁ ብላለች
አሜሪካ የሩሲያን መከላከያ ይደግፋሉ ባለቻቸው 42 የቻይና ኩባንያዎች ላይ የንግድ ገደብ ጣለች።
የአሜሪካ የንግድ ሚንስቴር የሞስኮን መከላከያና የውትድርና ግንባታ ይደግፋሉ ያላቸውን 42 የቻይና ኩባንያዎች በንግድ ገደብ መዝከቡ ማካተቱን አስታውቋል።
ዋሽንግተን ለሩሲያ ሚሳይሎችና ድሮኖች በግብዓት ይውላል ያለችው አሜሪካ ሰራሽ ሰርኩዊት ላይ ገደብ ጥላለች።
ንግድ ሚንስቴር በዩክሬን ንጹሃንን ኢላማ አድርገዋል ያላቸው መሳሪያዎች የሚጠቀሙትን ማይክሮ ኤሌክትሪክ ላይ ገደብ መጣሉን ገልጿል።
ሰባት የዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና የሌሎች ሀገራት ኩባንያዎችንም በቁጥጥር ዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
ሚንስቴሩ እርምጃው ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል ያለ ሲሆን፤ የአሜሪካ መሰረት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለሩሲያ ከላካችሁ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።
ዋሽንግተን ኩባንያዎችን በጥቁር መዝገቧ የምታካትተው ብሄራዊ ደህንነቷንና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን አስግቷል ብላ ስታምን ነው።
በዚህም አቅራቢዎች በዝርዝሩ ውስጥ ለተካተቱ ኩባንያዎች እቃዎችን ለመሸጥ ፈቃድ ማግኘት እንደ ሰማይ ሩቅ እንደሚሆንባቸው ይነገራል።
በዋሽንግተን የቻይና ኤምባሲ እርምጃው ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ ወዲያውኑ ምላሽ አለመስጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዋሽንግተን ውሳኔ የተላለፈው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን በተቃረበበት ጊዜ ነው።
ሀሙስ ዕለት ሩሲያ በዩክሬን አንድ መንደር ባደረሰችው የሚሳይል ጥቃት 52 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።
ጥቃቱ 20 ወራትን በደፈነው የጦርነቱ ታሪክ ገዳይ ከተባሉ ጥቃቶች ውስጥ ተመድቧል።