በፕሬዝዳንት ራይሲ ላይ ተቃውሞ ያላቸው ዜጎች በፕሬዝዳንቱ ሞት መደሰታቸውን የሚገልጽ ምልክት ቢያሳዩ ጥብቅ ቅጣት ይጠብቃቸዋል
በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ያለፈው የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እ የሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት የአስክሬን ሽኝት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ዛሬ ረፋዱ ላይ በተጀመረው የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርአት የሄሊኮፕተር ግጭቱ በተከሰተበት አቅራቢ በምትገኝው ታብሪዝ ከተማ በክፍት ተሸከርካሪ ላይ የሟቾች አስክሬን ተቀምጦ በከተማዋ እየተዘዋወረ ሽኝት ተደርጎለታል።
በታብሪዝ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢራናዊያን ጥቁር ለብሰው አስክሬኑን አጅበው በከተማዋ ሲዘዋወሩ ተስተውለዋል።
ቀጥሎም ወደ ዋና ከተማዋ ቴሄራን ያመራ ሲሆን በዛም በክቡር ዘቡ የክብር አቀባበበል ተደርጎለታል።
በነገው እለት በታላቁ ሞሳላህ መስጂድ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት የስንብት እና ሀይማኖታዊ ጸሎት ፕሮግራም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ሀሙስ ደግሞ ሀይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ሀሚኒ በሚታደሙበት ቅዱስ በተባለችው ማሻድ ከተማ ኢማም ረዛ ሸሪን የቀብር ስፍራ የሚያመራ ስለመሆኑ የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ኢማም ረዛ ሸሪን የቀብር ስፍራ ታላለቅ የሚባሉ የፐርሸያ ጀግኖች አስክሬን የሚያርፉበት ነው ባለፉት አመታትም በርካታ ጎብኝዎች ስፍራውን ጎብኝተውታል።
የኢራን ሀይማኖታዊ አስተዳደደር ለ5 ቀናት የሀዘን ቀን አውጆ የመንግስት መስርያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እስከ አርብ ድረስ የሚቆየውን የስንብትና የሽኝት ስነስርአት እንዲታደሙ አዟል።
በፕሬዝዳንት ራይሲ ላይ ተቃውሞ ያላቸው ዜጎች በፕሬዝዳንቱ ሞት መደሰታቸውን የሚገልጽ ምልክት ቢያሳዩ ጥብቅ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም መመሪያ ወርዷል።
የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት እንዲሁም ከፍተኛ ባለስልጣናት ሀዘናቸውን ሲገልጹ በአንጻሩ የሀዘን መልዕክት ለመላክ አሻፈረኝ ያሉም አልጠፉም።
እስካሁን በቀብር ስነስርአቱ ላይ የሚታደሙ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮቻቸው በግልጽ አልታወቁም ፡፡
የፕሬዝዳንት ራይሲን ህልፈት ተከትሎ የአደጋው ምርመራ እስካሁን በመጣራት ላይ ቢገኝም ከአደጋው ጀርባ አሜሪካ እና እስራኤል እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡
ይህ በቀጣይ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እንዲሁም ቴሄራን ከዋሽንግተን ጋር ሊኖራት የሚችለውን ግንኙነት ወሳኝ በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰቡ ጉዳዩን በአንክሮ በመከታተል ላይ ይገኛል
የ63 አመቱ የቀድሞ የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በፈረንጆቹ 2021 በተካሄደ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን፤ የሀይማታዊ መሪው አያቶላ ሀሚኒ ቀጣይ ተተኪ ሊሆኑ እንደሚችልም ሲነገር ሰንብቷል።