“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር ወደ ኬንያ ይደርሳል”- የኬንያው ፕሬዝዳንት
ዊሊያም ሩቶ በአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ የሚደረግ የሰላም ሂደት መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል
ፕሬዝዳንት ሩቶ ኡሁሩ ኬንያታን “የኢትዮጵያና የዲ.አር.ሲ የሰላም መልዕክተኛ” አድረገው መሾማቸውን ይታወሳል
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስባቸው ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከፍራንስ-24 ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር ወደ ኬንያ ይደርሳል” ያሉት ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ፤ ግጭቱ መፍተሄ እንዲያገኝ ኬንያ የራሷን ሚና ትጫወታለች ብለዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉበት የሰላም መልዕከተኛ አድረገው መሾማቸው ተናግረዋል፡፡
ዊሊያም ሩቶ፤ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት መፍትሄ ማግኘት በሚቻልበት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎሳ፣ ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ እና ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክን መወያየታቸውም አስታውቋል፡፡
በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና ኡሁሩ ኬንያታ እና ሁሉም ተዋናዮች ድጋፍ ታክሎበት፤ በአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ የሚደረግ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ጦረነት የሰው ልጆች ህይወት እየቀጠፈ ያለና ለቀጠናው አደጋ በመሆኑ ሁሉንም ወገኖች በተቻለ መጠን ወደ ጠረጴዛው ማምጣት አለብንም ነው ያሉት ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ፡፡
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀናት በፊት በነበረው በዓለ ሲመታቸው በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚቀጥሉ መናጋራቸው ይታወሳል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ድጋሚ መቀስቀስን ተከትሎ ተዋጊ ኃይሎችን ከማደራደር ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የኡሁሩ ኬንያታ ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
በተለይም አሁን ላይ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመሰደራደር ዝግጁ መሆናቸው የሚገልጸው ህወሓት፤ ከመንግስት ጋር በሚደረገው ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ይልቅ ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያሸማግሏቸው በተደጋጋሚ በይፋ ጠይቆ እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ለሚካሄደው ጦርነት መፍትሔ በመፈለጉ በኩል የአፍሪካ ህብረት ቀዳሚው አሸማጋይ ሊሆን እንደሚገባ ቀደም ሲል በያዘው አቋም እንደጸና መሆኑ ይታወቃል።