መድረክ ከአባሉ ኢሶዴፓ ለተነሳበት ቅሬታ ምን መልስ ሰጠ?
የኢሶዴፓ ሊቀመንበር በየነ (ፕ/ር) “በመድረክ ውስጥ ከኦፌኮ ጋር መስራት አስቸጋሪ” እንደሆነ ገልጸው ነበር
የመድረክ ሊቀመንበር መረራ (ፕ/ር) “መድረክ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ የወሰነው በአብላጫ ድምጽ ነው” ብለዋል
የመድረክ ሊቀመንበር መረራ (ፕ/ር) “መድረክ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ የወሰነው በአብላጫ ድምጽ ነው” ብለዋል
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረቡን ገልጾ ነበር፡
ነሀሴ 23 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው “ምርጫ 2012” በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ተከትሎ፣ ቀጥሎ ምን መደረግ አለበት በሚለው ገዳይ ላይ ገዥውን ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አማራጭ ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡
መድረክም የራሱን አማራጭ አቅርቢያለሁ ብሏል፡፡ነገርግን የመድረክ ጥምረት አባል የሆነውና በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የቀረበውን ሰነድ እንደማያውቀው ገልጿል፡፡
የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የኢሶዴፓ ሊቀመንበር በየነ (ፕ/ር ) ከጥቂት ቀናት በፊት በመድረክ ስም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደተላከ የተገለጸው ሰነድ ፓርቲያቸውን እንደማይወክል ለአል ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በየነ (ፕ/ር) በቃለ ምልልሳቸው “በመድረክ ውስጥ ከኦፌኮ ጋር መስራት አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ) እና የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) መድረክ አማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ የወሰነው በአባል ድርጅቶቹ መካከል በተደረገ ውይይት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱም መሰረት በአብላጫ ድምጽ እንደተወሰነ የገለጹት መረራ (ፕ/ር) የኢሶዴፓ ሊቀመንበር በየነ (ፕ/ር) መቃወማቸውንና ሌሎች የመድረኩ አባል ፓርቲዎች ግን በሃሳቡ ስለመስማማታቸው ለአል ዐይን አማርኛ አረጋጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት በድርጅት ደረጃ አራቱ ሲደግፉት አንዱ ማለትም ኢሶዴፓ መቃወሙን መረራ(ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡
መረራ(ፕ/ር) በድርጅት ደረጃ አራት ለአንድ በተወካዮች ደረጃ ደግሞ ስምንት ለአንድ በአብላጫ ድምጽ አማራጭ ሀሳቡ እንዲቀርብ እንደተወሰነ ተናግረዋል፡፡
“የኢሶዴፓ ሊቀመንበር አይወክለንም ብለው ለምን እንዳመለከቱ አላውቅም፣ምናልባት ሰዎች ከእኛ ጋር አለመስማማታቸውን እንዲያውቁላቸው ይሆናል” ያሉት መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ሌሎቹ የኢሶዴፓ አባሎች ጉዳዩን ይቃወሙ ወይም አይቃወሙ እንደሆነ እርግጠኛ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ድጋፍ የሰጡት ፓርቲዎች ሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አረና)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) እና የአፋር ፍትህ ፓርቲ ሲሆኑ ኢሶዴፓ ግን ተቃውሟል ብሏል መረራ (ፕ/ር)፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተልኳል የተባለው ሰነድ ይዘት ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው (ፕ/ር) መረራ አሁን ላይ ለሀገሪቱ ይበጃል ብለው የሚያምኑት የህግ ክርክር ሳይሆን የፖለቲካ ስምምነት ጉዳይ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
“ይህ የአንቀጽ ጉዳይ አይደለም ይተረጎማል የተባለውን በተመለከተም የአንድ ቡድን ደጋፊዎች ስለሆኑ የጥቅም ግጭት ያመጣል የሚሻለው የፖለቲካ ስምምነት ነው፣ ይህ የትርጉም ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚፈልጉት ነገር ይረዳዋል፡፡እኛ ግን ወደ ፖለቲካ ስምምነት እንሂድ የሚል ደብዳቤ ነው ያስገባነው” ብለዋል፡፡
በመድረክ ዕይታ “ወሳኝ ሊባሉ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት የሚስማሙባቸውን ጉዳዮች የሚፈጽም እንድ የሆነ አካል መፈጠር አለበት” ያሉት የመድረኩ ሊቀ መንበር ይህም የፖለቲካ፣ የሀገር፡ የህግ የበላይነት ጉዳዮችን የሚመለከት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
መረራ (ፕ/ር) መንግስትና ተቃዋሚን፣መንግስትና ህዝብን የሚያጋጩ ጉዳዮች መቆጣጠርና አቅጣጫ ማስያዝ የሚችል፣የጋራ አመራር የሚሰጥና የፖለቲካና ጸጥታ ጉዳዮችንም የሚያይ የጋራ የሆነ አካል እንዲቋቋም የሚጠይቅ ይዘት ያለው ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መላኩን አረጋግጠዋል፡፡
ይሁንና ከአራት ቀን በፊት ይህን ደብዳቤ እንደማያምኑበት የገለጹት የኢሶዴፓ ሊቀመንበርና የጥምረቱ (መድረክ) ምክትል ሊቀመንበር በየነ(ፕ/ር) ፓርቲያቸው የራሱን መግለጫ ማውጣቱንና በቀጣይ ከኦፌኮ ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚቸገር በዚህም ምክንያት ስብሰባ እንደሚያስፈልግ አስታውቀው ነበር፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የመድረኩና የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ይህ ጉዳይ “የሊቀመንበሩ ችግር ይመስለኛል፣ሌሎቹ ከምንጊዜውም በላይ ከእኛ ጋር እየሰሩ ነው፡፡ ኮንግረንሱ አስፍቶ ለመሄድ የሚሰራቸውን እንቅስቃሴዎች የኢሶዴፓ ሊቀ መንበር የወደዷቸው አይመስለኝም ” ብለዋል፡፡
ኦፌኮ ምርጫው ውስጥ በጋራ ለመግባትና የተሻለ የተቃዋሚ ህብረት ለመፍጠር በማሰብ ኦነግና ኦብነግ ጨምሮ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር በሚል ሃሳብ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከሦስትና አራት ወራት በፊት ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው እንደነበር ያነሱት የኦፌኮ ሊቀ መንበር በየነ (ፕ/ር) ያኔ በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተመሳሳይ ሃሳቦችን አንጸባርቀው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ስብሰባን በተመለከተ “ዝም ብለን አንድ ሰው ባኮረፈ ቁጥር ጉባዔ መጥራቱ አይጠቅምም ማለቴ ነው፣ብዙ ወጭ ያስወጣል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የመድረክ ሊቀመንበር ከሕግ ይልቅ የፖለቲካ መፍትሔ ይፈለግ ሲሉ ምክትሉ ደግሞ ሃገርና ህዝብ ደህንነት ሲባል አሁን ያለውን የሕገ መንግስት ትርጉም ማየቱ ይሻላል በሚሉ ሃሳቦቻቸው ቀጥለዋል፡፡