በቀጣይ ጊዜያትም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የደስታ መግለጫ ልከዋል።
ፕሬዝዳንቱ የደስታ መግለጫውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቴሌግራም ማድረጋቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
- በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ
- ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት ናት- በጠ/ሚ ዐብይ በበዓለ ሲመት የተገኙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች
ፕሬዝዳንት ፑቲን በመልእከታቸው አክለውም፤ የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት በመልካም የወዳጅነት ባህል እና የጋራ መከባባር ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደ መንግስት መሪነታቸው ወደፊት በሚያደርጓቸው ተግባራት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች የሚያጠናክር እንደሚያደርገውም እምነት አለኝ ብለዋል።
በዚህ ወቅት የሚኖረው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነትም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሁም በአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋትን የሚያመጣ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመልእክታቸው አክለውም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስኬትን እና መልካም ጤንነትን ተመኝተዋል።
ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ ሲሆን፤ በእለቱም የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በዓለ ሲመታቸው በመስቀል አደባባይ መካሄዱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የደስታ መግለጫ መላካቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝደንት ሼክ ክሃሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ የዩኤኢ ምክትል ፕሬዝደንት፤ ጠቅላይ ሚኒስትርና የዱባይ ገዥ ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም እንዲሁም የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም የደስታ መግለጫ ልከዋል።