“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር ምንም አይነት ድርድር አይኖርም”- ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ
ስርአተ ትምህርትም ከገበያው አንጻር ታይቶ እንደሚስተካከል ገልጸዋል
ፕሬዝዳንቷ “ለዓመታት የሕዝባችንን አንድነት አደጋ ላይ የጣሉና ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ሰንኮፎች በብሔራዊ መግባባት ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል
በኢትዮጵያ ለዓመታት የሀገርን ህልውና የሕዝብን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንዲሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ “ሰንኮፎች በብሔራዊ መግባባት” ሊፈቱ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንቷ የዛሬውን የአዲስ መንግስት ምስረታ መርሐ ግብር ተከትሎ በጋራ ለተሰበሰቡት የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2014 ዓ.ም የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫን አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የወጭ ንግድን 5 ነጥብ 25 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መታሰቡንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት ምስረታ እተካሄደ ነው
ባሳለፍነው ዓመት “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከ20 ዓመታት በላይ ሀገሩን በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲያገለግል በነበረው የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ አስነዋሪ ክህደትና ጭፍጨፋ መፈጸሙ ያልታሰበና አሳዛኝ ነበር” ያሉት ፕሬዝዳንቷ በሀገሪቱ ሌሎች አካባቢዎች ጽንፈኞች በፈጸሙት ጥቃት በርካቶች መሞታቸውንና መፈናቀላቸውንም ተናግረዋል፤ወደ ቀያቸው ቶሎ እንዲመለሱና እንዲያገግሙ ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡ በዚህ ዓመትም ይህን ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
“ወደድንም ጠላንም ተለዋጭ አገር የለንም፤ ያለን አማራጭ ተቻችለን መኖር ነው”ያሉት ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊያውያን ከምርጫው በኋላ የሚፈጽሟቸው በርካታ ተግባራት በመኖራቸው በጋራ መስራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ፤ ብሔራዊ መግባባት ይፈጠር ዘንድ “ሆደ ሰፊነት፣ መተማማን መተባበርና የውይይትና የክርክር ባህል ማዳበር” እንደሚገባ ያነሱ ሲሆን ብሄራዊ መግባባት “ነጠላ ጉዳይ ሳይሆን ረዥም ጊዜ የሚፈልግ” በመሆኑ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በትምህርት ዘርፍ በሁሉም ደረጃዎች ለሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ ትምህርት ለማዳረስ እንደሚሰራ በንግግራቸው ያነሱት ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ፤ የሀገሪቱ ስርአተ ትምህርትም ከገበያው አንጻር ታይቶ እንደሚስተካከል አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የሀገረ መንግስት ታሪኳ ሉአላዊነቷን አስደፍራ እንደማታውቅ የገለጹም ሲሆን “የነጻነት ምልክት ሆና አሁንም ትቀጥላለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ ብሔሯ “በደም የተጻፈን ታሪክ የብዕር ቀለም ሊለውጠው አይችልም” ያሉ ሲሆን “በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር ምንም አይነት ድርድር” እንደማይኖርም አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምትገኝበት አካባቢ የሃያላን ሀገራት ፍጥጫ እየጨመረ ስለመምጣቱ የገለጹት ርዕሰ ብሔር ሣሕለ ወርቅ በዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ተመልካች ልትሆን እንደማይገባ አንስተዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች መካከል ሁሉን አቀፍ ትብብርና ትስስር ለመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ፎረም እንደሚመሰረትና ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተቃኘ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሀገር መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮ እንዲኖሩ እነደሚሰራም ሣህለወርቅ ገልጸዋል፡፡