በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ
ወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር አይኖራትም ብለዋል
ምክክሩ በፖለቲካ ልሂቃን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ባካተተ መልኩ በኢትዮጵያውያን እየተመራ እንደሚካሄድም ገልጸዋል
በኢትዮጵያ በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ዛሬ እለተ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እና በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተካሂዷል።
“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር ምንም አይነት ድርድር አይኖርም”- ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበዓለ ሲመቱ ባደረጉት ንግግር “እልፍ ጀግኖችን ካፈራው የኢትዮጵያ ህዝብ በመፈጠሬ ሁሌም እንድኮራ ከሚያደርገኝ ውስጥ የህዝባችን አትንኩኝ ባይነት እና አይበገሬነት ነው” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ በማንነቱ የማይደራደር መሆኑ እሙን ነው”ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት ትሻለች ፤ድጋፍ በፈለገች ጊዜ ከጎኗ ለቆማችሁና ለደረሳችሁላት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
“ወደፊት የሚጠብቀን ተስፋ የሚበልጥ እንጂ አያንስም፤ ዋናው ጥያቄ ምን ያህል ቁርጠኝነት አለን የሚለው ነው፤ ኢትዮጵያ የምትበለፅገው እና ሀገራችንን ለመለወጥ በፈለግነበት ልክ ነው” ያሉ ሲሆን፤ “ኢትዮጵያ ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በንግግራቸው አክለውም፤ 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ምንም እንኳን “ከእንከኖች ሁሉ የጸዳና የምኞታችንን ያህል እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም” የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዲሞክራሲያዊ ስዓትን የመትከልና የማጽናት ህልም እውን ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ወደፊት አንድ እርምጃም አራምዶናል ብለዋል።
ህዝባችን ምርጫውን በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ጫናዎችን ተቋቁሞ ትልቅ ድልን አስመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል።
“በመጪው ዘመን ብዝሃነታንን እንደ ጌጥ ተቀብለን፤ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ይዘን ወደ ከፍታ እንተማለን፤ ለዚህም አካታች ብሄራዊ የምክክር መድረክ እናካሂዳለን” ብለዋል።
የምክክር መድረኩ በፖለቲካ ልሂቃን መካካል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ባካተተ መልኩ ሀገር በቀል ኢትዮጵያውያን መፍትሄ እየተመራ ይካሄዳል ሲሉም ተናግረዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንደ ሀገር ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ጠላት ብረት አንስቶ እንደ ብሌናችን የምናየውን የሰሜን እዝ አጠቃ፤ የጥሞና ጊዜ እንስጥ ባልንብት ጊዜም ህጻናትን እያስታጠቀ በርካታ ዜጎቻችንን አጠቃ፤ ንብረትም አወደመ ሲሉም በንግግራቸው አንስተዋል።
በበዓለ ሲመቱ ላይ የየትኞቹ ሃገራት መሪዎች ተገኙ?
“እኛ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ ይዘን ስንዘምትም ሆነ ሰይፍ ይዘን ስነነሳ ጠባችን ኢትዮጵያ ጠል ከሆኑት ጋር ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤ ኢትዮጵያ የተማሏ አቅም እና አቋም ያለው የፀጥታ ሀይል ታደራጃለች” ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እያስተናግድን ያለው የዲፕሎማሲ ጫና ወደኋላ ተመልሰን እንድንመለከት አስገድዶናል፤ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት አጥብቃ ትሻለች፤ ነገር ግን ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር አይኖራትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል አፍሪካ በዓለም መድረክ ራሷን ችላ እንድትቆም እና ችግሮቿን በራሷ እንድትፈታ በማድረግ ረገድ የበኩሏን መወጣቷን አበክራ ትቀጥላችም ብለዋል።
ህዳሴ ግድብን በተመከለተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው፤ የህዳሴ ግድብ ቀጠናዊ ትስስር እና መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
“ዓባይ ማለት የመነሳታችን ምሳሌ፤ በራሳችን አቅም መቆሚያ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ“ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቆርጦ ተነስቷል፤ ያጠናቅቃልም” ብለዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲያደርግ እናደርጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣታቸውን በማስታወስ መንግስት በቀጣይ ዓመታት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶት የዋጋ ንረትን መግራት ላይ ይሰራል ብለዋል።