የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ ያልተገኙት የቻይናው ፕሬዝዳንት ከሩሲያ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል
ሩሲያ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ የናዚ ሽንፈት 80ኛ ዓመት በዓል አዘጋጅታለች
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/10/258-152601-whatsapp-image-2025-02-10-at-2.25.36-pm_700x400.jpeg)
ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ ያልተገኙት የቻይናው ፕሬዝዳንት ከሩሲያ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል፡፡
ሩሲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር በሚመራው የናዚ ጦር ላይ የተቀዳጀችውን ድል በየዓመቱ ግንቦት ላይ ታከብራለች፡፡
አውሮፓዊያን ይህንን የቸድል በዓል በፈረንጆቹ ግንቦት 8 ቀን ሲያከብሩት ሩሲያ ደግሞ አንድ ቀን ዘግይታ ታከብረዋለች፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን የዘንድሮው የድል በዓል በደማቁ እንዲዘጋጅ አዘዋል የተባለ ሲሆን ከወዲሁ እንግዶች እንዲገኙ ጥሪ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
በድል በዓሉ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት የዓለም መሪዎች መካከል የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ አንዱ ናቸው ተብሏል፡፡
እንደ ሩሲያው ታስ ዘገባ ከሆነ ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ በሞስኮ እንዲገኙ ያቀረበችላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ከአንድ ወር በፊት ዋሸንግተን እንዲገኙ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢጋበዙም ምክትላቸውን ልከው ነበር፡፡
ይህም ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ከአሜሪካ ይልቅ ለሩሲያ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ማሳያ ነው የሚል አረዳድ ፈጥሯል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ቤጂንግ በመከባበር እና ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ብቻ እንደሚተገብር አስታውቋል፡፡
ሩሲያ የናዚ ጦር ሽንፈት 80ኛ ዓመት በዓልን ከዚህ በፊት ከነበሩት ለየት ባለ መንገድ እንደምታከብር የገለጸች ሲሆን በዓሉ ከዩክሬን ጦርነት ጋር እንደሚገናኝም ተገልጿል፡፡