የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ሩሲያን ሊጎበኙ ነው
የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ሞስኮ እና ቤጂንግ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ግንኙነታቸው እንዳልሻከረ ለማመላከት ያለመ ነው ተብሏል
ቻይና ባለፉት አስር አመታት የሩስያ ትልቅ የንግድ አጋር ሆናለች
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ሩሲያን እንደሚጎበኙ ሞስኮ አስታወቀች፡፡
የፕሬዝዳንት ሺ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ "ትልቅ ክስተት" ተደርጎ የሚወሰድ እንደሚሆንም መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገው ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ቤጂንግ ጉብኝቱን በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር ባይኖርም የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ታህሳስ ወር ባደረጉት የቪዲዮ ጥሪ የቻይና አቻቸው ሞስኮን እንዲጎበኙ ጋብዘው እንደነበር አይዘነጋም።
ሁለቱም መሪዎች ባሳለፍነው መስከረም ወር በኡዝቤኪስታን የሻንጋይ የትብብር ድርጅት መሪዎች ጉባኤ ላይ ተገናኝተው የነበረ ቢሆንም ፤ አንዱ የአንዱን ሀገር ከጎበኘ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
እናም የፕሬዝዳንት ሺ የሩሲያ ጉብኝት በ2019 በሴንት ፒተርስበርግ ተዘጋጅቶ ከነበረው የሶስት ቀናት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በኋላ የሚደረግ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጉዞ ይሆናል ተብሏል፡፡
የሩሲያው የዜና ወኪል /ታስ/ እንደዘገበው ከሆነ "ሞስኮ እና ቤጂንግ በዚህ አመት በሁለቱ መንግስታት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ " ይሆናል፡፡
"ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበርና ህጋዊ መስመርን በመከተል አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ የበላይነትን ለማስገኘት የምታደርገውን ጥረት ለመዋጋት ተከታታይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሰርተናል" ያለው የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፤ በነበረው ሂደት የቻይና ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ገልጿል፡፡
አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ቻይና የሩሲያ “ወዳጅ ሀገር ናት” ሲልም አሞካሽቷታል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
ሞስኮ እና ቤጂንግ የውጭ ፖሊሲዎቻቸውን በማስተባበር በአስደናቂው የጂኦፖለቲካዊ ለውጦች ውስጥ ሆነው “ዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማስጠበቅ፣ ቀጠናዊ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ግጭቶችን ለማሸነፍ እና የጋራ የትብብር አጀንዳዎችን ለማስቀጠል” ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸውም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የጂንፒንግ የሞስኮ ጉብኝት ዜና የተሰማው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሳምንቱ መጨረሻ ከቻይና አቻቸው ጋር በቤጂንግ ሊገናኙ በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ነው፡፡
ቻይና ከአስር አመታት በላይ የሩስያ ትልቋ የንግድ አጋር ሆና መዝለቅ ችላለች፡፡
በተለይም ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ፤ የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ ለቻይና ነዳጅ በማቅረብ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች።
የቻይናው ፕሬዝዳንት በሞስኮ ጉብኝት ያደርጋሉ የተባለው በሩሲያ የጸደይ ወቅት በሚጀምርበት መጋቢት ወር ነው፡፡