አሜሪካ ከቻይና ጋር ጦርነት የመግጠም አቅም እንደሌላት ተገለጸ
አሁን ላይ አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ከቻይና ጋር ወደ ጦርነት ብታመራ ከአንድ ሳምንት በላይ መዋጋት እንደማትችል ተገልጿል
የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች በበቂ መጠን እያመረቱ አይደለም ተብሏል
አሜሪካ ከቻይና ጋር ጦርነት የመግጠም አቅም እንደሌላት ተገለጸ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት በየጊዜው እየሻከረ መጥቷል።
አሜሪካ ቻይና የሀይል የበላይነቴን ለመውሰድ እየተጋች ነው በሚል በይፋ በስጋትነት ከፈረጀቻት ዓመታትን ያስቆጠር ሲሆን ይሄንን ተከትሎም ሁለቱ ሀገራት ፍጥጫቸው እንደቀጠለ ነው።
የንግድ ጦርነት፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች ፉክክሮች የቀጠለ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ውጥረቱ ከፍ ብሏል።
ዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ባወጣው ጥናት መሰረት አሜሪካ አሁን ላይ ከቻይና ጋር የመዋጋት አቅም እንደሌላት ዎልስትሪት ጆርናል ጥናቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በጥናቱ መሠረት አሜሪካ ያላትን የተለያዩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን መለገሷ የጦር መሳሪያ እጥረት እንደገጠማት ተገልጿል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የጀመረችውን ጦርነት በድል እንድትወጣ በሚል በየጊዜው ለኪቭ የተለያዩ መሳሪያዎችን ሰጥታለች።
ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች በፍላጎቱ ልክ እያመረቱ አለመሆናቸው ለዋሸንግተን ካዝና መራቆት በምክንያትነት ተጠቅሷል።
አሁን ላይ አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደ ጦርነት ብታመራ ከአንድ ሳምንት በላይ መዋጋት እንደማትችል ተቋሙ በጥናቱ ላይ ጠቅሷል።
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ስትነጻጸር በወታደራዊ ቴክኖሎጂ መስክ አምስት እጥፍ ቀድማ መሄዷን የጠቀሰው ይህ የጥናት ማዕከል ዋሽንግተን ለጉዳዩ ትኩረት እንድትሰጥ አሳስቧል።
አሜሪካ ለዩክሬን ከመጋዝኖቿ እያወጣች ለዩክሬን ከሰጠቻቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች መካከል የአጭር እና ሙካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎች፣ የአየር መቃወሚያዎች እና ወታደራዊ አውሮፕሎኖችን ከግለሰብ ትከሻ ላይ ተተኩሶ መምታት የሚችለው ከስምንት ሺህ በላይ ጃቪየር ሚሳኤል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።