ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ እና ቻይና ጦር ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርግ አስታወቀች
የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ በደቡብ አፍሪካዋ የወደብ ከተማ ደርባን ላይ ይካሄዳል ተብሏል
የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች የጋራ ወታደራዊ ልምምዱን ተችተዋል
ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ እና ቻይና ጦር ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርግ አስታወቀች።
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ሀይል እንዳስታወቀው ከቻይና እና ሩሲያ ጦር ጋር ልምምድ ለማድረግ አቅዷል።
ከፈረንጆቹ የካቲት 17 እስከ 26 ቀን 2023 ድረስ የሚካሄደው ይህ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ልምምድ በሀገሪቱ የወደብ ከተማ በሆነችው ደርባን ላይ እንደሚካሄድ የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
350 የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች እንደሚሳተፉ የተገለጸው ይህ የጋራ ጦር ልምምድ ፕሪቶሪያ ከሞስኮ እና ቤጂንግ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት የበለጠ ያጠናክረዋል ተብሏል።
"ኦፕሬሽን ሞሲ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህን ወታደራዊ ልምምድ የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ተቃውመውታል።
ፖለቲከኞቹ የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ ደቡብ አፍሪካ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ ገለልተኛነቷን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ብለዋል።
አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ደቡብ አፍሪካ በይፋ ሩሲያን እንድታወግዝ ግፊት ያደረጉ ቢሆንም ሀገሪቱ እስካሁን አላወገዘችም።
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት የሚመሰርቱ የአፍሪካ ሀገራትን እቀጣለሁ ማለቷን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ዋሽንግተን የአፍሪካን ፍላጎት እንድታከብር ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጊ ላቭሮቭ የፊታችን ሰኞ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚጓዙ ተገልጿል።
ደቡብ አፍሪካ የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ ለመገዳደር የተቋቋመው የብሪክስ መስራች እና አባል ሀገር ናት።
በምህጻረ ቃሉ ብሪክስ የሚባለው የአምስት ሀገራት ስብስብ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን በአባልነት ይዟል።