የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ እስራኤል በዩክሬን ጦርነት ያላትን ገለልተኝነት ተቹ
ዘለንሰኪ እስራኤል ኪቭን አለመደገፏ ለሩሲያ እና ኢራን ወታደራዊ አጋርነት አድል ፈጥረዋል ብለዋል
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እስራኤል በግጭቱ ውስጥ ከሩሲያ ወይም ዩክሬን አንዳቸውን እንድትመርጥ ጠይቋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እስራኤል በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ያላትን ገለልተኝነት ተቹ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የእስራኤል መሪዎች ኪቭን ላለመደገፍ መወሰናቸው ሩሲያ ከኢራን ጋር ያላትን ወታደራዊ አጋርነት የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ዘለንስኪ የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር ;እስራኤል የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በሩሲያ ጥቃት እየተፈጸመባት ያላትን ዩክሬን ወታደራዊ ርዳታ ለመስጠት ብትስማማ ኖሮ በሞስኮ እና በቴህራን መካከል ትብብር አይፈጠረም ነበር ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ፖለቲከኞቻችሁ በዚያን ጊዜ አንድ ውሳኔ ብቻ ቢወስኑ ኖሮ ይህ የእነርሱ ጥምረት በቀላሉ ሊከሰት አይችልም ነበር ... ከረጅም ጊዜ በፊት የተወሰነ ይመስላል - በ2014 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራዋን ስትጀምር” ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
አክለውም " 'ክሬምሊንን ላለማስከፋት' እና ዩክሬንን በትክክል ላለመርዳት የተደረገው ውሳኔ " በሞስኮ እና በቴህራን መካከል ጥምረት እንዲፈጠር አስችለዋል ብለዋል፡፡
እንደፈረንጆቹ የካቲት 24 ሩሲያ ጎረቤቷን ከወረረች በኋላ እስራኤል የሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመጥለፍ የሚረዱ ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ለዩክሬን ወታደራዊ ዕርዳታ ላለመስጠት ጥብቅ ፖሊሲዋን ጠብቃ ቆይታለች።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ ያለው የኢየሩሳሌም አቋም ከገለልተኝነት ሩሲያን የበለጠ ወደ ማውገዝ እንደተሸጋገረ ይነገራል፡፡
ነገር ግን ለዩክሬን የምታደርገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሌለ እስራኤል አሁንም ግልጽ አድርጋለች፡፡
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ በትናንትናው እለት ለዩክሬን አቻቸው ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ “እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ስርዓት አትሰጥም” ማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
እስራኤል በዩክሬኑ ጦርነት ያላትን አቋም ግልጽ ብታደረግም ግን ለኪቭ ሰዎች የሚዋጥ አልሆነም፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እስራኤል በግጭቱ ውስጥ ምርጫ እንድታደርግ ጠይቋል፡፡
“ የመንግስታችሁ ውግንና ከማን ጋር እንደሆነ ለመምረጥ ጊዜው አሁን አይደለምን?” ሲሉም ነው የተደመጡት ፕሬዝዳንቱ፡፡