ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ሶስት እጩዎች ከፕሬዝዳነት ሲሲ ጋር እየተፎካሩ ነው
በግብጽ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት በዛሬው እለት መካሄድ ጀመረ።
የጀመሪያ ዙር የድምጽ አሰጣት ስነ ስርዓቱ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን እስከ ፊታችን ማክሰኞ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብፃውያን ሀገራቸውን ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራውን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ወደ ምርጫ ጣያዎች በመሄድም ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የመጀመሪያ ዙር ድምጽ የመስጠት ሂደት መጀመሩን ተከትሎ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በዛሬው እለት በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምጽ ሰጥተዋል።
- ግብጽ በታህሳስ ወር በምታደርገው ምርጫ ፕሬዝዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል
- “የግብጽ ጦር ጠንካራ አቅም ካላቸው ሃያል የመካከለኛው ምስራቅ ጦሮች መካከል አንዱ ነው”-አል ሲሲ
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲን ጨምሮ አራት እጩዎች በእጩነት ቀርበዋል።
ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲን የሚፎካከሩት ሶስቱ እጩዎችም የሪፐብሊካን ህዝቦች ፓርቲ መሪ ሀዚም ኦማር፣ የግብፅ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ፋሪድ ዛህራን እና የዋፍድ ፓርቲ መሪ አብደል-ሳናድ ያማማ መሆናቸውም ተነግሯል።
በዛሬው እለት በተጀመረው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ላይ 65 ሚሊየን ግብጻያን በ20 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 10 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ዛሬ የተጀመረው የድምጽ አጣጥ ሂደት እስከ ፊታችን ማክሰኞ ታህሳስ 2 ድረስ ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንት ሰኞ ታህሳስ 8 የመጀመሪያው የምርጫ ውጤት ይፋ ይደረጋል።
በምርጫው ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ዳግም ይመረጣሉ ተብሎ በሰፊው ይጠበቃል።
68 ዓመታቸውን የያዙት ሲሲ በ2019 በተደረገ የህገ-መንግስት ማሻሻያ ለሦስተኛ ዘመን መወዳደር እንደሚችሉ መደረጉ ይታወሳል።
የህገ-መንግስት ማሻሻያው አራት ዓመት የነበረውን የአንድ የስልጣን ዘመን ወደ ስድስት ዓመት ከፍ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ፕሬዝዳንት አል ሲሲ እስከ 2030 ድረስ መንበሩ ላይ እንዲቆዩ በር ከፍቷል።