ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቁን አስታወቁ
ጉባዔው “ለአህጉራችን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት ነበር” ብለዋል
35ኛ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ “በሰላም እና በስኬት” መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ለሁለት ዓመታት ከተቋረጠ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ “የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል” ብለዋል።
“የኅብረቱ ጉባኤ ፍሬያማ ውይይት የተካሄደበት፣ ለአህጉራችን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ ከምንም በላይ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት ነበር ማለት ይቻላል” ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመግለጫው አክለውም፤ “ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ወዳጅ ስትፈልግ ከማንም ቀድማችሁ ደርሳችሁልናል፤ ሌሎች ሲሸሹን ከጎናችን በመቆም እውነተኛ ወዳጅነታችሁን አስመስክራችኋል፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ከልብ ታመሰግናችኋለች” ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሁለሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "የአፍሪካ የሥርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ኃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማትን ያፋጥናል" በሚል መሪቃል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል።
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ሴኔጋል የ2022 የህብረቱን ሊቀመንብርንት ስፍራን ከየዴሞክራቲ ክሪፐብሊክ ኮንጎ ተረክባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በዓለም አቀፉ መድረክ ድምጿ የሚሰማበት ተገቢ ውክልና ይገባታል ብለዋል።
በተመድ 70 ዓመት ታሪክ አፍሪካ አሁንም እንደ ጀማሪ አጋር ነው የምትታየው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ 2 ቋሚና 5 ተለዋጭ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ማለታቸውም ይታወሳል።