የፍልስጤም ደጋፊዎች ተቃውሞ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፋ ነው
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከ100 በላይ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ በኒውዮርክና የል ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው እንዲጠናከር አድርጎል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ጸረ ሴማዊ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉትም ሆነ ፍልስጤማውያን ያሉበትን ሁኔታ የማይረዱ” አካላትን አውግዘዋል
የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እየበረታ የመጣውን የተማሪዎች ተቃውሞ ለማብረድ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት የተቃወሙ ከ100 በላይ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተቃውሞውን ወደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እያሰፋው ነው ተብሏል።
ፖሊስ ትናንት ምሽት በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን ተቃውሞ ለማስቆም በመግባት በርካታ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል።
በየል፣ በርክሌይ፣ ማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ኤምአይቲ) እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎች ማደሪያቸውን በዳስ አድርገው ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን፥ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ እንግዶች እንዳይገቡ በሩን ዝግ አድርጓል።
108 ተማሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲም የገጽ ለገጽ ትምህርት አቁሟል።
ተማሪዎቹ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው እንዲያወግዙ እንዲሁም ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ጠይቀዋል።
የፍልስጤም ደጋፊዎች በእስራኤል ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ያስተላለፏቸው “ጸረ ሴማዊ መልዕክቶች” ግን እስራኤላውያን ተማሪዎችን ስጋት ውስጥ መጣሉን ነው አሶሼትድ ፕርስ የዘገበው።
አይሁዳውያን ተማሪዎች የፍልስጤሙ ሃማስ አሁንም ድረስ እስራኤላውያንን አግቶ መያዙንና ከ1 ሺህ 100 በላይ እስራኤላውያንን ህይወት መቅጠፉን ያነሳሉ።
ቁጥራቸው አነስ ይበል እንጂ እስራኤላውያን ተማሪዎችም በኮሎምቢያ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ድምጻቸውን አሰምተዋል ተብሏል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ የተማሪዎቹን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከር ከመሆን ይልቅ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ላይ መጠመዳቸው ተቃውሞውን እያስፋፋው መሆኑ ተገልጿል።
በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፋ ስለመጣው የተማሪዎች ተቃውሞ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፥ ጸረ ሴማዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች መተላለፋቸውን ተቃውመዋል።
ፕሬዝዳንቱ “በፍልስጤም ምን እየተካሄደ እንደሆነ የማያውቁ” ያሏቸውን ወገኖችም ተቃውመዋል።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር በሆነችው አሜሪካ የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በርካታ የአደባባይ ተቃውሞዎች ቢደረጉም ዋሽንግተን በቴል አቪቭ ዙሪያ የማይነቃነቅ አቋም እንዳላት የ26 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በማጽደቅ አሳይታለች።