ለመርሳት በሽታ የተጋለጡ ሙያተኞች የትኞቹ ናቸው?
በሹፍርና ሙያ የተሰማሩ ሰዎች ከሌሎች ሙያዎች አንጻር ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው ተብሏል
በመላው ዓለም ከ55 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመርሳት በሽታ ጋር እንደሚኖሩ ተገልጿል
ለመርሳት በሽታ የተጋለጡ ሙያተኞች የትኞቹ ናቸው?
የመርሳት በሽታ የሰዎች አዕምሮ መታወክ ሲሆን በቀስ በቀስ ሰዎች የማስታወስ እና የማሳብ ችሎታቸውን ሲያጡ የሚከሰት ህመም እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ማስታወስ አለመቻል፣ የቋንቋ አጠቃቀም መለወጥ፣ የባህሪ ለውጦች፣ ጣዕሞችን ለመለየጥ መቸገር፣ ጥየቄዎችን መደጋገም፣ የተለመዱ ዕለታዊ ስራዎችን መስራት አለመቻል ወይም ቀላል ስራዎችን ለመስራት ረጅም ጊዜ መውሰድ ደግሞ ከበሽታው ምልክቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የሀርቫርድ ህክምና ትምህርት ቤት ከሰሞኑ በመርሳት ወይም አልዛይመር በሽታ ዙሪያ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ጥናት መሰረት የማስታወስ ችሎታዎችን ሊያሳድጉ በሚችሉ ሙያዎች ዙሪያ የተሰማሩ ሰዎች በመርሳት በሽታ የመጠቃት እድላቸው አነስተኛ ነው ብሏል፡፡
ጥናቱ በ443 የስራ አይነቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን ከሁሉም በሹፍርና ሙያ የተሰማሩ ሰዎች ለመርሳት በሽታ በአንጻራዊነት አነስተኛ የመጋለጥ እድል እንዳላቸው ጠቅሷል፡፡
ለአብነትም ስራቸው የግድ ከማስታወስ እና ልዩ የአዕምሮ ንቃት የሚጠይቁ ሙያዎች ለምሳሌ ሹፌሮች ከሌሎች ሙያዎች ጋር ሲነጻጸር በመርሳት በሽታ የመጠቃት እድላቸው ይቀንሳል፡፡
በተለይም የከተማ ትራንስፖርት የሚሰጡ ሾፌሮች ማሳለጫ እና መታጠፊያ መንገዶችን ስለሚያውቁ፣ የግድም ሁሉንም መንገዶች ማወቅ ስላለባቸው አዕምሯቸው ሁሌም ንቁ እንዲሆን መገደዳቸው በዚህ በሽታ የመጠቃት እድሉን እንደሚቀንስላቸው ተገልጿል፡፡
በለንደን የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች በአውሮፕላን፣መርከብ እና አውቶቡስ ማሽከርከር ላይ ከተሰማሩት ጋር ሲነጻጸሩ ለመርሳት በሽታ ያላቸው ተጋላጭነት አነስተኛ እንደሆነ ይሄው ጥናት አሳይቷል፡፡
ከሁሉም ደግሞ የአምቡላስ ሹፌሮች አዕምሯቸው የበለጠ ንቁ እንዲሆኑ ስራቸው ስለሚያስገድድ ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከሌሎች ተመሳሳይ ሾፌሮች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በመላው ዓለም 55 ሚሊዮን ዜጎች ከመርሳት በሽታ ጋር ይኖራሉ የተባለ ሲሆን የተጠቂ ሰዎች ቁጥርም በየዓመቱ እየጨመረ ነውም ተብሏል፡፡