የቋንቋ መምህሩ ለተማሪዎች የምታሳየው ፍቅር የማረከው ወጣት “እድሜ ቁጥር ብቻ ነው” ብሎ ከብዙ ድካም በኋላ ምኞቱን ማሳካቱን ገልጿል
ሙሃመድ ዳኔል አህመድ አሊ በፈረንጆቹ 2016 የማሌዥያ ቋንቋ አስተማሪውን ጀሚላህ ሞህድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከት የ15 አመት ታዳጊ ነበር።
በወቅቱ ምንም የተለየ የፍቅር ስሜት እንዳልተሰማው የሚያነሳው ሙሀመድ ዳኔል፥ ታዳጊም ቢሆን ጀሚላ ለተማሪዎች የምታሳየው ፍቅርና እንክብካቤ እየረሳኝም ይላል።
ከክፍል ክፍል ሲዛወር የቋንቋ አስተማሪውን ያጣው ሙሃመድ፥ በ2017 በአጋጣሚ ወደ መምህራን ቢሮ ሲያመራ ጀሚላን ያገኛትና ሰላምታ ሰጥቶ ያልፋል።
ከዚህ በኋላ ስለጀሚላ ማሰብ ማንሰላሰል ጀመርኩ የሚለው ሙሀመድ፥ የልደት መልካም ምኞት ከጀሚላ ሲደርሰው ነገሮች ሁሉ በፍጥነት መልካቸውን መቀየራቸውን ያስታውሳል።
በአጭር የጽሁፍ መልዕክቱ የተጀመረው ንግግርም እያደገ ሄዶ የታዳጊነት ስሜቱን ሳይደብቅ በ26 አመት ለምትበልጠው የቀድሞ መምህሩ የፍቅር ጥያቄ ማቅረቡን ለማሌዥያው ኒው ስትሬት ታይምስ ይናገራል።
ጀሚላም የእድሜ ልዩነታቸውን በመጥቀስ በፍጹም የማይሆን ነገር ነው የሚል ምላሽ ትሰጣለች።
“አድራሻዋን አላውቅም ነበር፤ እድል ቤቷ ድረስ ወሰደኝ” የሚለው ሙሀመድ፥ ቤት ውስጥ ሁሉንም ነገር በግልጽነት እንዳወሩም ነው የሚገልጸው።
ያም ሆኖ ጀሚላ በአቋሟ መጽናቷን ተከትሎ ወጣቱ ሙሀመድ ለረጅም ጊዜ መወትወቱንና ለማሳመን መጣሩን ይገፋበታል።
መምህርት ጀሚላ የቀድሞ ተማሪዋ ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ ማለቱን ስትመለከት ከሁሉ ነገር ቀድሞ የሚመጣው የእድሜ ልዩነታቸው ጉዳይ እየደበዘዘ ይሄዳል።
“ወደኔ ሲመጣ በሙሉ መተማመን ነው፤ ለቤተሰቦቹም ሲያሳውቅ አላፈረም፤ ይህ ይበልጥ እንድተማመንበት አድርጎኛል” የምትለው ጀሚላ፥ ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አቋሟን እንድለውጥ እንዳደረጋትም ትናገራለች።
እናም ለቤተሰቦቻቸው አሳውቀው ጋብቻቸውን ለመፈጸም መስማማታቸውን ታስታውሳለች።
በ2021 በጋብቻ ለመጣመር የያዙት እቅድም በኮሮና ምክንያት ተራዝሞ ከሰሞኑ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው በተገኙበት በመጠነኛ ሰርግ ተሞሽረው የማሌዥያ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው ሰንብተዋል።
“እድሜ ቁጥር ብቻ ነው፤ እንደ ባል የሚጣልብኝን ሃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል የ22 አመቱ ወጣት።
በፈረንጆቹ 2007 የመጀመሪያ ባሏን የፈታችው ጀሚላም ስራዋ ላይ ትኩረት አድርጋ ለወንዶች ሁሉ ዘግታው የነበረውን ልቧን ለባለቤቷ ሙሀመድ ዳኔል ክፍት ማድረጓን መናገሯ ተዘግቧል።