የበረራ ህግ ጥሰዋል በተባሉት ስድስት ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ
ፖሊስ እነዚህን ግለሰቦች በሽብር ወንጀል እና ከጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ጠርጥሮ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን ገልጾ ነበር
የተከሳሾቹ ጠበቃ ዋስትና እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም ፍርደ ቤቱ በዋስትና ጉዳይ ብያኔ ለመስጠት ጉዳዩን ለመስከረም 7፣2016 ዓ.ም ቀጥሮታል
የበረራ ህግ ጥሰዋል በተባሉት ስድስት ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአውሮፕላን ውስጥ የበረራ ህግ የሚጥስ ተግባር ፈጽመዋል በሚል ታሰረው የነበሩት ስድስት ግለሰቦች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ኢቢሲ እንደዘገባው በእነዮሐንስ ዳንኤል የክስ መዝገብ የተካቱት ስድስት ግለሰቦች በሶስት ነጥቦች ተከሰዋል።
የፌደራል ፖሊስ ባለፈው ነሐሴ ወር ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቀሌ ለመሄድ እየተዘጋጀ በነበረ አውሮፕላን ውስጥ "ሁከትና ግርግር" ፈጥረዋል በሚል እነዚህን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን መግለጹ ይታወሳል።
ፖሊስ በዚሁ መግለጫው እነዚህን ግለሰቦች በሽብር ወንጀል እና ከጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ጠርጥሮ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን ገልጾ ነበር።
አንደዘገባው ከሆነ አቃቤ ህግ አውሮፕላንን አላግባብ በመያዝ፣ በኮምፒውተር በመታገዝ ስም በማጥፋት እና የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን እንዳይፈጽሙ በማወክ በሚሉ ሶስት ነጥቦች ነው የተከሰሱት።
በተከሳሽ ግለሰቦች እና በአየርመንገዱ የደህንነት ሰዎች መካከል የተፈጠረውን እሰጣገባ የሚያሳዩ ቪዲዮች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀው መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
በቪዲዮው ውስጥ እነዚህ ግለሰቦች ከአውሮፕላኑ "አንወርድም" ሲሉ እና የደህንነት ሰራተኞቹ ደግሞ "ወረዱ" መሄድ አይቻልም እያሉ ሲጨቃጨቁ ተደምጠዋል።
እሰጣገባው የተፈጠረው የደህንነት ሰራተኞች አውሮፕላኑ መብረር እንደማይችል መግለጻቸውን ተከትሎ ነበር።
ክስ የተመሰረባቸው ተጠርጣሪዎች ዮሀንስ ዳንኤል፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤሊያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና ኢሌኒ ክንፈ ናቸው።
በቲክቶክ የሚታወቀው እና የመዝበጉ መጠሪያ የሆነው ዮሐንስ በሶስቱ ነጥቦች ሲከሰስ ሌሎቹ አምስቱ ደግሞ በሁለቱ ነጥቦች መከሰሳቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ ዋስትና እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም ፍርደ ቤቱ በዋስትና ጉዳይ ብያኔ ለመስጠት ጉዳዩን ለመስከረም 7፣2016 ዓ.ም ቀጥሮታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ በነሐሴ 16፣2016 ባወጣው መግለጫ ስለመቀሌው በረራ በቀጥታ ባይጠቅስም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ለበረራ መሰረዝ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል።