በብፁዕ አቡነ ማቲያስ ጉዞ ወቅት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተፈጠረው ምንድነው?
ፓትሪያርኩ የያዟቸው ታቦታት በቤተክርስቲያኗ ዕውቅና እና ሕጋዊ አሠራርን የተከተለ ነው- ብፁዕ አቡነ አብርሃም
ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና ከፓትሪያርኩ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም- የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ትናንትና ለህክምና ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ተከትሎ የተለያዩ ጉዳዮች እየተሰሙ ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ወደ ውጭ ለመሄድ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ “ቅርስ ይዘው ነበር”፤ “አልያዙም ውሸት ነው” የሚል ክርክር በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲንጸባረቅ ነበር፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በአቡነ ማቲያስ ጉዞ ወቅት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የነበረውን የፍተሻ ሂደት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲኗ እና ከፓትሪያርኩ ጋር ማገናኘት ትክክል አይደለም ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ቅርሶች በሀገር ሀብትነት የተመዘገቡ በመሆናቸው ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ስለሚስፈልጋቸው መከታተል የግድ እንደሆነና ይህም የተቋሙ የአሰራር አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ይህንን ጉዳይ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና ከፓትሪያርኩ ጋር ማገናኘት አይገባም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የሀገር መሪዎችም ሆኑ ሌላ አካል ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ ከተቋሙ የማሳወቂያ ደብዳቤ እንደሚወሰድ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በቤተ ክህነት የተለመደ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በተቋሙ አሰራር መሰረት ከታቦት/ ጽላት/ በስተቀር ቅርስ ከኢትዮጵያ ውጭ ሊቀመጥ የሚችል ቅርስ እንደሌለ ያነሱት አበባው አያሌው፤ የሚሄደው ቅርስ የሚመለስበት ጊዜ አብሮ ይቀመጣል ብለዋል፡፡
ለምርምር፤ ለአውደ ርዕይም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ከሀገር የሚወጣ ማንኛውም ቅርስ መቸ እንደሚመለስ ጭምር ቀነ ገደብ ይቀመጥለታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ስራው በጥንቃቄ የሚሰራ ነውም ብለዋል፡፡
በቅርስነት የተመዘገቡም ያልተመዘገቡም ቁሶች ከሀገር መውጣት የሚችሉት የባለስልጣኑን ማረጋገጫ ሲያገኙ ብቻ እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ቅርስ ባይሆኑም አዳዲስ የመጾር መስቀሎች፤ ከብር ከነሃስ፤ ከወርቅ የተሰሩ የእጅ መስቀሎች ከሀገር መውጣት እንደማይችሉም ነው አበባው አያሌው ለአል ዐይን አማርኛ ያስታወቁት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ትናንትና ለህክምና ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በተገኙበት ወቅት አብረዋቸው ሊጓዙ የነበሩ “ህገ ወጥ ቅርሶች ተያዙ” በማለት የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን ቤተ ክርስቲኗ ገልጻለች፡፡
አቡነ ማቲያስ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሲነሱ የያዟቸው ቅርሶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ፊርማ የተፈቀዱ መሆኑንም ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሰጡት መግለጫ ፤ አቡነ ማትያስ ወደ ውጭ ሀገር የሄዱት ቀደም ሲል ባስታወቁት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው ይህም በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የፓትሪያርኩ ጉዞ ሕጋዊና ምክንያቱ የሕክምና ክትትል ለማድረግ መሆኑን የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የሚያውቀት እንደሆነም ነው አቡነ አብርሃም የተናገሩት፡፡
ቅዱስነታቸው ሊወስዷቸው የነበሩ ታቦታት በቤተክርስቲያኗ ዕውቅና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ጽ /ቤት ትዕዛዝ በቅርፃ ቅርፅ ክፍል ተዘጋጅቶ ይዘውት እንዲሄዱ የተዘጋጀ የተለመደና ሕጋዊ አሠራርን የተከተለ መሆኑን አቡነ አብርሃም ገልጸዋል፡፡
በጉዞው ወቅት ቅርጻ ቅርጽ የሚለውን "ቅርሳ ቅርስ" በማለት የተፈጠረው ውዝግብ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል።