ተፈጥሮን መጠበቅ አለምን ከ2 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ይታደጋል- የአለም ባንክ
የባንኩ ጥናት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት በ2030 በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸውን 10 በመቶውን እንደሚያጡ አመላክቷል
የአለም ባንክ የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ስራዎች የሚያቀርበውን ብድር ወደ 9 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል
ተፈጥሮን ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች መጠበቅ አለምን በ2030 ከ2 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ያድናል አለ የአለም ባንክ።
በባንኩ የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሃብቶችዳይሬክተር ቫለሪ ሂኪ ከኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በሀገራት ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ተጎጂ መሆናቸውን በመጥቀስ ሀገራቱ በ2030 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው (ጂዲፒ) ውስጥ 10 በመቶውን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደሚያጡ በጥናት መረጋገጡን አብራርተዋል።
- 140 ሚሊየን ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስደተኛ ይሆናሉ - የአለም ባንክ
- የዓለም ቢዝነስ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ 5 ቢሊዮን ዶላር አዋጡ
ደኖች እና የውሃማ አካላትን ብዝሃ ህይወት መጠበቅ ካልተቻለ የሀገራት ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ክፉኛ እንደሚፈተንም ነው የጠቆሙት።
በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የሚደርሰው አደጋ በሰው ልጆች ጤና፣ ምግብ ዋስትና፣ የሃይል ፍላጎት እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖው እየበረታ ስለሚሄድ ሀገራት ተፈጥሮን ለመጠበቅ መትጋት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
የአለም ባንክም ተፈጥሮን መጠበቅ ለመሰረተ ልማት ማስፋፋትም ሆነ ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ መሆኑን በማመን የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በኮፕ28 ጉባኤ የአለም ባንክም የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ስራዎች የሚያቀርበውን ብድር በ2024 እና 2025 ወደ 9 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
ሌሎች አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለማቅረብ ከስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው።