ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት በኦልድትራፎርድ እንደሚካሄድ ይጠበቃል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የክለቦች እግር ኳስ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይጀምራል።
በኢትዮጵያ ከሚወደዱ ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል አንዱ የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ምሽት ይጀምራል።
ከሶስት ወራት እረፍት በኋላ የሚጀምረው ይህ እግር ኳስ ውድድር በማንችስተር ዩናይትድ እና ፉልሀም መካከል በይፋ የ2024/25 ውድድር ይጀምራል።
አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው የኤሪክ ቴንሀጉ ማንችስተር ዩናይትድ ፉልሀምን በቀላሉ ሊያሸንፍ እንደሚችል በርካቶች ቢገምቱም የፉልሀሙ አሰልጣኝ ማርኮስ ሲልቫ በመክፈቻ ጨዋታዎች ጥሩ የሆነ ያለመሸነፍ ሪከርድ አላቸው።
በነገው ዕለት በርከት ያሉ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ኢፕስዊች ከሊቨርፑል፣ አርሰናል ከወልቭስ፣ ኤቨርተን ከብራይተን ፣ ኒውካስትል ከሳውዛምፕተን ቀን ላይ ከስምንት ሰዓት ጀምሮ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
እሁድ ደግሞ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ ቸልሲን ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ይገጥማል።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ብሬንት ፎርድ ከክሪስታል ፓላስ እሁድ ከሚደረጉ ጨዋታዎች አንዱ ነው።
የ2024/25 ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነሀሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ተጀምሮ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የውድድር መርሀ ግብሩ ያስረዳል።