ብሪታንያ ለዩክሬን የላከቻቸው የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቀደች
የሩሲያን ድንበር ጥሶ የገባው የዩክሬን ጦር "ቻሌንጀር 2 " የተሰኘውን የብሪታንያ ታንክ እየተጠቀመ ነው ተብሏል
ሩሲያ ምዕራባውያን ለኬቭ የላኩት የጦር መሳሪያ ግዛቷን አልፎ ጥቃት እንዳያደርስ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች
ብሪታንያ ለዩክሬን የላከቻቸው የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መፍቀዷ ተነገረ።
የሩሲያን ድንበር ጥሶ የገባው የዩክሬን ጦር "ቻሌንጀር 2 " የተሰኘውን የብሪታንያ ታንክ እየተጠቀመ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ለማድረስ የትኞቹን የለንደን የጦር መሳሪያዎች መጠቀም እንዳለባት ከመናገር ተቆጥቦ ቆይቷል።
የዩክሬን ጦር ባለፈው ሳምንት የሩሲያን ድንበር ጥሶ ከገባ በኋላ ግን ኬቭ ብሪታንያ የላከችላትን የጦር መሳሪያዎች የመጠቀም ሙሉ መብት አላት ብሏል።
ዩክሬን በሩሲያ ምድር በጀመረችው ውጊያ ብሪታንያ የላከችላትን ፀረ ታንክ ሚሳኤሎች፣ ታንኮችና ሌሎች ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መጠቀም እንደምትችልም ነው ያስታወቀው።
ኬቭ "ስቶርም ሼዶው" የተሰኘውን ሚሳኤል በሩሲያ ግዛት ውስጥ መጠቀም እንደማትችል ግን አሳስቧል።
በሀምሌ ወር በለንደን ጉብኝት ያደረጉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከአውሮፕላን ላይ የሚተኮሰው "ስቶርም ሻዶው" ሚሳኤል ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት መደረጉን ገልፀው ምን ውሳኔ እንደተላለፈ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ብሪታንያ ምዕራብ ሰራሽ ታንኮችን ለኬቭ በመሰላክ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን በ2023 14 "ቻሌንጀር 2" ታንኮችን መላኳ ይታወሳል።
የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ግዛት እያካሄደው ባለው "ዘመቻ" የአሜሪካ እና ጀርመን ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑ ተዘግቧል።
ሩሲያ ምዕራባውያን ለኬቭ የላኩት የጦር መሳሪያ ግዛቷን አልፎ ጥቃት እንዳያደርስ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
የብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ ጀርመንና ሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ጥቃት ለማድረስ መዋላቸውም ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ "ቅይጥ ጦርነት" መክፈታቸውን ያረጋግጣል ብለዋል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ።
ክሬምሊን ከ200 ሺህ በላይ ሩሲያውያንን እንዲፈናቀሉ ምክንያት ለሆነችው ዩክሬንና ለተባባሪዎቿ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።