የኢፌዴሪ አየር ሀይል “ጠላት” ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ምርጥ ኢላማዎች በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን ገለጸ
የትግራይ ክልል ር/መስተዳድር ኤርትራ ወረራ ፈጽማለች በማለት የገለጹ ሲሆን ውንጀላቸውን መከላከያ አጣጥሏል
ሰራዊቱ በአሁኑ ሰዓት ከሁመራ እስከ ሽራሮ ጥቃት በመፈጸም የተለያዩ ስፍራዎችን እየተቆጣጠረ ነው- ሜ/ጄ መሐመድ ተሰማ
የኢፌዴሪ አየር ሀይል “ጠላት” ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ምርጥ ኢላማዎች በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን ገለጸ
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄነራል ይልማ መርዳሳ ፣ አየር ኃይሉ “ጠላት” ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ምርጥ ኢላማዎች በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን አስታወቁ።
ለ”ጁንታው እስትንፋስ የነበሩ የነዳጅ ዴፖዎች ፣ የመሳሪያ ማከማቻዎች እና ሌሎች ምርጥ ኢላማዎችን ጀቶቻችን ያለምንም ከልካይ እንዳሻቸው እየተመላለሱ አውድመዋቸዋል” ብለዋል ።
”ፓይለቶቻችን የተመረጡ ዒላማዎችን ለመደምሰስ መሣሪያ ጭነው እየሄዱ ሲቪል የሚጎዳ ከመሰላቸው ሳይተኩሱ በመመለስ ነጥሎ የመምታት ስትራቴጂ እየተከተሉ ይገኛሉ” ሲሉም አስረድተዋል።
የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የጦር አውሮፕላን መትተው መጣላቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሜ/ጀ ይልማ በመግለጫቸው ”ጁንታው አውሮፕላን እንመታለን የሚለው ፣ እድሜውን ሲዋሽ ስለኖረ ባህሪው ነው” ያሉ ሲሆን “ባሻን ሰዓት እየተመላለስን ለህግ እስኪቀርብ ማጥቃታችንን እንቀጥላለን” ማለታቸውንም የመከላከያ ሰራዊት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በሰጡት መግለጫ ደግሞ ሁመራና አካባቢው ሙሉ ለሙሉ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።
ሰራዊቱ በአሁኑ ሰዓት ከሁመራ እስከ ሽራሮ ጥቃት በመፈጸም የተለያዩ ስፍራዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።
ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ የእርዳታ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተነጋግረው ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
በትናንትናው እለት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ በሁመራ እና በባድመ ግምባሮች የኤርትራ ሰራዊት በከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድብደባ በመፈጸም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግስትኤርትራ ድንበር ጥሳ ወረራ እንድትፈጽም አድርጓል ሲሉም ወንጅለዋል፡፡
ሜ/ጄ መሐመድ ግን የርዕሰ መስተዳድሩን መግለጫ አጣጥለዋል፡፡ ሕወሓት በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትን መለዮ በማዘጋጀት ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች በመግለጽ ህዝብን እያደናገረ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ጠይቀዋል።