የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር በአሜሪካ ኮንግረስ በሚያቀርቡት ንግግር ላይ በርካታ ዴሞክራቶች እንደማይገኙ ተገለጸ
ም/ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሃሪስን ጨምሮ የኮንግረሱ ኮሚቴ ሰብስቢ ዴሞክራቶች በጋዛው ጦርነት ምክንያት በኔታንያሁ ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል
በኮንግረሱ መሰብሰቢያ አካባቢ ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚቃወሙ ሰልፈኞች የጋዛውን ጦርነት መቆም የሚጠይቁ መፈክሮችን አስተጋብተዋል
ከሰኞ እለት ጀምሮ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የከተሙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
በዛሬው አለት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ጦርነቱ ስለሚገኝበት ሁኔታ እና አጠቃላይ አካባቢያው ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኔታንያሁኑ በስልጣን ዘመናቸው ለአራተኛ ጊዜ ለኮንግረሱ በሚያደርጉት ንግግር ከብሪታንያው ጠቅላይ ጠቅላይ ሚንስተር ዊንሰትን ቸርቺል በኋላ ለበርካታ ጊዜ በኮንገረሱ የተገኙ ቀዳሚው የውጭ ሀገር መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
ኔታንያሁ በካፒቶል ሂል ተገኝተው የሚያደርጉትን ንግግር ለመቃዎም በርካታ የማህበረሰብ አንቂዎች ያስተባበሩት የተቃውሞ ሰልፍ በአሁኑ ወቅት በኮንግረሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካባቢ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ሰልፈኞቹ ጠቅላይ ሚንስትሩ የጦርነት ማቆም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንዲሁም ታጋቾችን እንዲያስለቅቁ በተጨማሪም የንጹሀን ፍልስጤማውያን ሞት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኮንግረሱ በሚያቀርቡት ንግግር የአሜሪካ እና እስራኤል ትብብር በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖረውን ሚና ፣ በጋዛ ያለው ጦርነት ወደ ቀጠናዊ ግጭት መሻገር ያለውን አደገኛነት እንዲሁም በኢራን እና ሂዝቦላ ላይ የሚደረገው ጫና እና ማዕቀብ ጠንከር ማለት እንደሚገባው ሀሳባቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በዴሞክራት የኮንግረስ እና ሴኔት አባላት በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በምክር ቤቱ ንግግር የሚያደርጉት ኔታንያሁ የዴሞክራቶች አስተዳደር ጦርነቱ በቶሎ እንዲቋጭ ለእስራኤል በቂ ድጋፍ አላደረገም በሚል ነው፡፡
ሆኖም ኔታንያሁ በሃሳብ ልዩነት ውስጥ ከሚገኙት አሁናዊው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቀሪ የ6 ወራት የስልጣን ዘመን ለማግኝት ስለሚገባቸው የድጋፍ ሀሳብ ዴሞክራቶችን በማያስከፋ መንገድ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቶች እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የኔታንያሁ አስተዳደር በጋዛ በየቀኑ ለሚሞቱ ንጹሀን በቂ ጥንቃቄ አላደረገም በሚል ጠቅላይ ሚንስትሩን ከሚወቅሱ የባይደን አስተዳደር ሰዎች መካከል ዋነኛዋ ሲሆኑ በዛሬው የኮንግረሱ ስብሰባ ላይም እንደማይሳተፉ ታውቋል፡፡
ሁሉም የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ጥቂት የማይባሉ የዴሞክራት ፓርቲ የኮንግረስ አባለትም የኔታንያሁን ንግግር በኮንግረሱ ተገኝተው እንደማይከታተሉ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
ንግግሩን እንደማይካፈሉ ካሳወቁ ዲሞክራቶች መካከል አንዱ የሆኑት ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን “ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀገር ቤት ያጋጠማቸው ፖለቲካዊ ችግር በአሜሪካ ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው ለማስተካከል ማቀዳቸው ተገቢ አይደለም፤ ኔታንያሁ የአሜሪካን እና እስራኤልን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ለማስቀጠል ትክክለኛው ሰው አይደሉም” ብለዋል።