ሞስኮ ምርመራው እስኪጠናቀቅ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሏል
ክሬምሊን የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪ ይቭጂኒ ፕሪጎዚኒ በምዕራባዊያን በሞስኮ ትዕዛዝ ተገደሉ መባሉን አስተባበለ።
የምዕራባዊያን ፖለቲከኞች መሪውን ፑቲን እንዳስገደሏቸው ምንም ማስረጃ ሳይጠቅሱ ተናግረዋል።
ውንጀላውን "ፈጽሞ ውሸት" ነው ያለው ክሬምሊን፤ የዋግነርን መሪ ሞት ከማረጋገጥ ግን ተቆጥቧል። ሙሉ ምርመራው እስኪጠናቀቅ መጠበቅ አስፈላጊ ነውም ብሏል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፖስኮቭ ይህን ውንጀላና ተመሳሳይ ክሶችን ውሸት ናቸው ብለዋል።
የሩሲያ አየር ባለስልጣን ረቡዕ ዕለት የዋግነር መሪና ሌሎችም መንገደኞች ያሳፈረ የግል አውሮፕላን ሞስኮ አቅራቢያ መከስከሱን ተናግሯል። በአደጋውም የተረፈ ሰው እንደሌለ አረጋግጧል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአደጋው ማዘናቸውን ለቤተሰቦቻቸው ሲገልጹ፤ ፕሪጎዚኒን "ነበሩ" እያሉ ተናግረዋል። ይህም ፕሪጎዚኒ ከሩሲያ ጦር ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ ከሁለት ወራት በኋላ ፑቲን በቀጥታ ዝምታቸውን ሲሰብሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ስለ መሪው ጀግንነት ያወደሱት ፑቲን፤ ጥፋት መስራታቸውንም አልሸሸጉም።