የዋግነር ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ሩሲያ ዋግነርን በአዲስ ስያሜና መሪ ዳግም ወደ ተልዕኮው ትመልሰዋለች ወይስ ተዋጊዎቹን ወደ መደበኛ ጦር ትቀላቅላለች?
ክሬምሊን እስካሁን በዋግነር እጣ ፈንታ ዙሪያ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል
የዋግነር ቅጥረኛ ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በአውሮፕላን አደጋ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ የቡድኑ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።
ክሬምሊን በዋግነር ዙሪያ እስካሁን ግልጽ ያለ አቋሙን ይፋ አላደረገም።
ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭም ከህግ አንጻር ህልውና እንደማይኖረው ቢጠቅሱም “አሁን ምንም ማለት አልችልም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዋግነር በሩሲያ ወታደራዊ አመራሮች ላይ አውጆት የነበረው አመጽን በሀገር ክህደት የተመለከቱት ፕሬዝዳንት ፑቲንም እስካሁን ስለቡድኑ ቀጣይ እጣ ፈንታ ያሉት ነገር የለም።
ተንታኞች ግን ሞስኮ በተለያዩ ሀገራት ስታሰማራው የቆየችውን ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ታፈርሳለች ብለው አያምኑም።
ዋግነር ማን ነው?
ምስረታውን በፈረንጆቹ 2014 ያደረገው ዋግነር በሺዎች የሚቆጠሩ ልምድ ያላቸውና አልሞ ተኳሽ ተዋጊዎችን ማፍራት ችሏል።
ከወታደራዊ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ፣ በደህንነት ቢሮዎች ውስጥ የሰሩ፣ በቼቼን ጦርነት የተሳተፉ እና በወንጀል ተፈርዶባቸው የታሰሩ ሰዎችንም መልምሎ ወታደሮቹ አድርጓል።
ቡድኑ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን ከእስር ቤት ሲመለምል በጦር ሜዳ ጀብዷቸው በምህረት እንደሚለቀቁ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጭምር እንዳረጋገጡለት ይገልጽ ነበር።
የ62 አመቱ ይቪግኒ ፕሪጎዥን ለፑቲን ምግብ ከማብሰል ተነስተው ዋግነርን የመሰለ በወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ የፈረጠመ ቡድን ሰርተዋል።
በ2014 በዩክሬን የተሰጠውን ተልዕኮ መፈጸም ጀምሮም በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ደቡብ አሜሪካ ፈጥኖ የሚደርስ የሩሲያ ሃይል ሆኗል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ስታውጅም ዋግነር የባክሙቱን ውጊያ ከጅማሮ እስከ ፍጻሜ አድርሷል።
በእነዚህ ዘጠኝ አመታት ውስጥ ቅጥረኛ ወታደራዊ ሃይሉ ያሳየው ብቃት ሞስኮ ከመሪው ፕሪጎዥን በኋላ እንዲፈርስ ትፈቅዳለች ወይ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።
የሰኔ 23ቱ አመጽ
በዩክሬን በመሳሪያ አቅርቦት ችግር ተዋጊዎቼ እያለቁ ነው ያለው ዋግነር ሞስኮ ድረስ ዘልቆ የሩሲያ መከላከያ አመራሮችን ለማስወገድ አምጽ ቀስቅሶ ነበር።
ሬስቶቭ የተባለች ከተማን ይዞ ወደፊት ለመገስገስ ሲዘጋጅ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የዋግነር መሪ የነበሩትን ይቪግኒ ፕሪጎዥን ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር አደራድረው ለ24 ስአት የቆየው ውጥረት ረገበ።
ይህ አመጽ በማንኛውም ወታደራዊ ዘመቻ ከፑቲን ውጭ ትዕዛዝ አልቀበልም የሚሉትን ፕሪጎዥን ከሞስኮ የጦር ሹማምንት ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ከባድ ቁርሾ ውስጥ መክተቱ ይታወሳል።
አመጹ የዋግነር ተዋጊዎች ከሩሲያ መከላከያ ጋር ውል እንዲፈራረሙ ውል ማሰር የማይፈልጉት ደግሞ በቤላሩስ በካምፕ እንዲቆዩ አድርጓል።
የፕሪጎዥን ህልፈትና የዋግነር ቀጣይ እጣ ፈንታ
በአዋጊ ግርማ ሞገሱ የሚሞካሹት ይቪግኒ ፕሪጎዥንን ጨምሮ 10 የዋግነር አመራሮች ባለፈው ሳምንት በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ሩሲያ በቀጣይ ስለቅጠረኛ ቡድኑ የምታሳልፈው ውሳኔ ይጠበቃል።
“ኢስተርን ሰርክል” የተባለ ተቋም መስራቿ አናስታሲያ ሻፖችኪና ከፍራንሥ4 ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሁለት ነገሮች ይጠበቃሉ ይላሉ።
የመጀመሪያው ዋግነርን በአዲስ ስያሜ እና አመራር ማደራጀትና የተለመደ ስራውን ማስቀጠል ነው። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ቡድኑን በሩሲያ ጦር ውስጥ ማካተት።
ሩሲያ ዋግነርን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ማስፈጸሚያ ታደርገዋለች፤ ዋግነር ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ያደረገው ስምምነትም ከፍተኛ ገንዘብ ያስገኛል” የሚሉት አናስታሲያ፥ ሞስኮ የዋግነር ህልውና ከፕሪጎዥን ህልፈት በኋላ ቢደበዝዝም እንዲጠፋ ግን አትፈልግም ባይ ናቸው።
የሰኔ ወሩ አመጽ ፑቲንን እና የሩሲያ ወታደራዊ ሹማምንትን ብዙ አስተምሯል የሚሉ ተንታኞች ደግሞ ዋግነር ከፕሪጎዥን ህልፈት ጋር ተቀብሯል የሚል እምነት አላቸው።