የዋግነር አመራሮችን ይዞ ስለተከሰከሰው አውሮፕላን ፕሬዝዳንት ፑቲን ምን አሉ?
ፕሬዝዳንት ፑቲን አደጋው ከደረሰ ከ24 ሰዓታት በኋላ ዝምታቸውን ሰብረዋል
ሰባት የዋግነር አመራሮችን ይዞ ሲበር የነበረ የግል አውሮፕላን ባሳለፍነው ረቡዕ ተከስክሷል
በሩሲያ በደረሰ የአውሮፐላን አደጋ የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ህይወት ሳያልፍ አልቀረም የሚለው ዜና አሁንም የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንደሆነ ቀጥሏል።
የዋግነር ሌሎች አመራሮችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የግል ጄት ከሞስኮ በስተሰሜን ተከስክሶ ሁሉም ተጓዦች ህይወታቸው አልፏል።
በዚህ በረራ ተጓዥ ከነበሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የፕሪጎዥንም ተካቷል መባሉን ተከትሎ ነው የዋግነር መሪው ህይወቱ አልፏል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ የሚገኙት።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ረቡዕ ከሞስኮ በስተሰሜን ስለተከሰከሰው አውሮፕላን ከ24 ሰዓታት በኋላ ዝምታቸውን ሰብረዋል።
ፑቲን በአውሮፕላን አደጋው ህይታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የዋግነር ቡድን መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን በአውሮፕላኑ ውስጥ ስለመኖራቸው ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
“የመጀመሪያ ሪፖርት እንደሚያመላክተው የዋግነር ኩባንያ ሰራተኞች በአውሮፕላኑ ውስጥ አሉ” ያሉት ፑቲን፤ “አደጋው በጣም አሳዛኝ ነው፤ እነዚህ ሰዎች በዩክሬን ያለውን የኒዮ-ናዚ አገዛዝ ለመዋጋት ለጋራ ጉዳያችን ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ ማስታወስ እፈልጋለሁ፤ በዚህ ስራቸው ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ” ብለዋል።
ፑቲን ስለ ዋግነሩ መሪ ሲናገሩም፤ “ይቪግኒ ፕሪጎዥን ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቼ ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ በህይወት አጋጣሚው አስቸጋሪ እጣ ፈንታ ያለው ሰው ነው፤ በህይወቱ ከባባድ ስህተቶችንም ሰርቷል፤ ለራሱ የሚፈልገውን ውጤት ለማግኘት ታግሏል” ብለዋል።
“እኔ እስከማውቀው ድረስ ፕሪጎዥን ከአፍሪካ ትናንት መመለሱን እና ከተወሰኑ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቶ እንደነበረ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ “ስለ አውሮፕላን አደጋው የቴክኒክ ኮሚቴው ሪፖርት አቅርቦልኛል፤ በአደጋው ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጀምረዋል፤ እስከ መጨረሻው በጥንቃቄ ይከናወናል፤ በዚህ ላይ ምንም ጥርጣሬ የለኝም” ብለዋል።
“መርማሪዎች በቅርቡ የሚሉንን እንጠብቅ፤ አሁን ላይ የቴክኒካል እና የጄኔቲክ (ዘረመል) ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው፤ ይህ ደግሞ የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል” ሲሉም ተናግረዋል።