ፒኤስጂ እና ምባፔን እያወዛገበ ያለው የ60 ሚሊየን ዶላር ጉዳይ
የፈረንሳይ እግርኳስ ሊጎች አስተዳዳሪው (ኤልኤፍፒ) ኪሊያን ምባፔ እና ፒኤስጂን ማሸማገል ሊጀምር ነው ተብሏል
ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ምባፔ ደመወዝና ጉርሻ አልተሰጠኝም ይላል፤ ፒኤስጂ ደግሞ ተጫዋቹ ጉርሻ እንደማይቀበል ተስማምቶ እንደነበር ይገልጻል
የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ጀርሜን (ፒኤስጂ) ከቀድሞ ኮከቡ ጋር የገቡበትን ውዝግብ የሀገሪቱ የእግርኳስ አስተዳዳሪ ተቋም (ኤልኤፍፒ) እየተመለከተው መሆኑ ተገለጸ።
ፒኤስጂ ተቋሙ ለወራት ስጠይቀው የነበረውን የማሸማገል ጥያቄ በመቀበሉ ደስተኛ ነኝ የሚል መግለጫን አውጥቷል።
የምባፔ ጠበቆችም የፈረንሳይ ሊግ አስተዳዳሪ በሚመራው ድርድር ውዝግቡ እልባት እንዲያገኝ ፍላጎት እንዳላቸው ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ፈረንሳዊው አጥቂ ባለፈው የውድድር አመት ማብቂያ ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ በኋላ ፒኤስጂ ሊከፍለኝ የሚገባው 60.58 ሚሊየን ዶላር ደመወዝና ጉርሻ ገቢ አልተደረገልኝም ብሏል።
የ25 አመቱ አጥቂ ለቀድሞ ክለቡ ቀሪ ደመወዝ እና ጉርሻ (ቦነስ) እንዲከፈለው በይፋ በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ ሲጠባበቅ መቆየቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
ይሁን እንጂ ፒኤስጂ የተጫዋቹን ጥያቄ በድርድር እንፈታዋለን ከማለት ውጭ እስካሁን መፍትሄ ሳይሰጠው ቆይቷል።
የክለቡ ቃልአቀባይ “ምባፔ በአደባባይ ደጋግሞ የተናገራቸውንና ቃል የገባቸውን ጉዳዮች ሊያከብርነ ለቃሉ ታማኝ ሊሆን ይገባል፤ በሰባት አመት ቆይታው ከክለቡ ያገኘውን ወደርየለሽ ጥቅምም ሊዘነጋው አየገባም” ብለዋል።
ምባፔ ባለፈው አመት ጥር ወር ከፒኤስጂ ሊቀመንበር ናስር አል ከላይፊ ጋር ሲወያይ ከክለቡ ጋር በሚለያይበት ወቅት የሁለቱም አካላት ክብርና ጥቅም እንዲጠበቅ ተስማምተው ነበር።
በወቅቱ መገናኛ ብዙሃን ምባፔ ከፒኤስጂ በነጻ ዝውውር የሚለያይ ከሆነ ቦነስ እንደማያገኝ ተስማምቶ እንደነበር ሲዘግቡ እንደነበር ይታወሳል።
የፒኤስጂ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪ ኪሊያን ምባፔ ለፈረንሳዩ ክለብ 308 ጊዜ ተሰልፎ 256 ጎሎችን አስቆጥሯል።