ነውጠኛው የፒ ኤስ ቪ ደጋፊ ለ40 አመታት ወደ ስታዲየም ድርሽ እንዳይል ታገደ
የሲቪያውን ግብ ጠባቂ ማርኮ ድሚትሮቪች ወደ ሜዳ ገብቶ ለመደባደብ የሞከረው የ20 አመት ወጣት የሶስት ወራት እስራትም ተፈርዶበታል
የኔዘርላንድሱ ክለብ የተጫዋቾችን ደህንነት ባለማስጠበቁ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል
ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን በአውሮፓ ሊግ ከሲቪያ ጋር የመልስ ጨዋታውን ሲያደርግ ወደ ሜዳ ዘሎ የገባውን ደጋፊውን ለአራት አስርት አመታት ወደ ስታዲየም እንዳይገባ አግዶታል።
የ20 አመቱ ደጋፊ ተጠባቂው የመልስ ጨዋታ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም።
በራሞን ሳንቼዝ ፒዥዋን ስታዲየም 3 ለ 0 የተሸነፈው ፒ ኤስ ቪ በሜዳው ፊሊፕስ ስታዲየም 2 ለ 0 እየመራ ባለበት ጊዜ ነው ስሙ ያልተጠቀሰው የፒ ኤስ ቪ ደጋፊ ወደ ሜዳ ዘሎ የገባው።
ደጋፊው የሲቪያውን ግብ ጠባቂ ማርኮ ድሚትሮቪች ፊቱን በጥፊ በመምታት ንዴቱን ለማቀዝቀዝ ቢሞክርም ድሚትሮቪች ከመሬት ጋር አጣብቆ አላንቀሳቅስ ብሎት በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ዲሚትሮቪች በጨዋታው 2 ጎሎች ቢቆጠሩበትም፤ ያልተጠበቀ የደጋፊ ድብደባን ቢያስተናግድም ክለቡ ሲቪያ በደርሶ መልስ ድምር ውቴት (3 ለ 2) አሸንፏል፤ ጨዋታውንም አጠናቆ በመውጣት ድሉን ከጓደኞቹ ጋር አጣጥሟል።
ለአንድ ወር ጉዳዩን ሲያጣራ የቆየው ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን ነውጠኛው ደጋፊ እስከ 2063 ወደ ስታዲየም እንዳይገባ ወስኗል።
ቀደም ብሎም በብሄራዊ ስታዲየም እንዳይገባ እግድ የተጣለበት ደጋፊው በጓደኛው አማካኝነት ትኬት አስገዝቶ አጭበርብሮ ወደስታዲየም መግባቱ ተገልጿል።
በቀጣይ ሁለት አመታት ስታድየም መግባት አይደለም በፒ ኤስ ቪ ፊሊፕስ ስታዲየም ዙሪያ መንቀሳቀስ አትችልም የሚል ውሳኔ የተላለፈበት ወጣት ስታዲየም ገብቶ ያሳየው ነውር ፒ ኤስ ቪን ከባድ ቅጣት ያስጥልበታል ተብሏል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በየካቲት 23ቱ የፊሊፕስ ስታዲየም ክስተት ዙሪያ የሚያደርገውን ማጣራት አጠናቆ በቅርቡ ቅጣቱን ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ፌነርባቼን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ የደረሰው የስፔኑ ክለብ ሲቪያ በበኩሉ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የሚፋለም ይሆናል።